የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የአርበኝነት ኅብረብሔራዊ መገለጫ ምልክት ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የአርበኝነት ኅብረብሔራዊ መገለጫ ምልክት ነው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የአርበኝነት ኅብረብሔራዊ መገለጫ ምልክት ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
17ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞችም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት ዕለቱን የሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ስርዓት በማካሄድ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በዚሁ ጊዜ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፥ ሰንደቅ ዓላማ ወሳኝ ሀገራዊ የሉዓላዊነት አሰባሳቢ ምልክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል የአርበኝነትና የኅብረብሔራዊ አንድነት መገለጫ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ለሠንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር መስጠት ማለትም የሀገርን ሉዓላዊ አንድነት ለማስጠበቅ ውድ ዋጋ ለከፈሉና ለሚከፍሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት እንዲሁም ቀደምት ጀግኖች አርበኞችን ማክበር እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚተጉ ብርቱ ክንዶችን ማክበርም ሌላኛው የሀገር ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ ማክበር መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ መልኩም ለሀገራቸው ሉዓላዊ ምልክት ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን በማሰብ ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የተከፈለውን ውድ ዋጋ በማስተማር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሠኞ የሚከበረው የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮም በፌደራል መንግስት፣ በክልል፣ በአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች ተቋማት፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ሥርዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር እና ሀገራዊ አንድነትን በሚያትቱ ጣዕመ ዜማዎች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።