ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017(ኢዜአ)፦ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የእንኳን ለ17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱ ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው ያለው አገልግሎቱ ኢትዮጵያውያን በደረሱበት የዓለም ክፍሎች ይዘውት የሚጓዙት ትልቁ ስንቅና ትጥቅ በልባቸው የተሳለው የሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ነው ሲል ገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው ስኬቶችና ድሎች ምሥጢሩ ከሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ጋር የተቆራኘ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ፣ የአፍሪካ የነጻነት ምልክትም ነው ሲል አስታውቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያስተላለፈው የመልካም ምኞት መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለ17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ!
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፤ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ለ17ኛ ጊዜ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ይከበራል፡፡
ዕለቱን በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቆመን ስናከብር ያለውን ትርጉምና ክብር በአግባቡ በመረዳት ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የጋራ ዓርማ ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምልክት፣ የጥንካሬያችን ሐውልት፣ የድላችን ዓርማ፣ የሉዓላዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የኅብረ ብሔራዊ አብሮነታችን ዋስትና መሆኑን በአግባቡ በመረዳት ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠት ይገባል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው። ኢትዮጵያውያን በደረሱበት የዓለም ክፍሎች ይዘውት የሚጓዙት ትልቁ ስንቅና ትጥቅ በልባቸው የተሳለው የሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ነው።
ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው ስኬቶችና ድሎች ምሥጢሩ ከሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ጋር የተቆራኘ ነው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ፣ የአፍሪካ የነጻነት ምልክትም ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን ክብሩና ዝናው ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያውን ዛሬም ሆነ ነገ እንደ ትናንቱ መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው፡፡
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰንደቅ ዓላማው እንዳትደፈርና የሀገሩ ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በጦር ሜዳ አጥንቱን የሚከሰክሰው፣ ደሙን የሚያፈስሰው ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ነው።
በደምና አጥንት ተጠብቆ የቆየውን የሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ሉዓላዊነታችንን ይበልጥ ማፅናት የሚቻለው በተሰማራንበት የሥራ መስክ ተግባራችንን በትጋት ስንከውን፣ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ስንታትር፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን በዓርበኝነት ስሜት ስንዋጋ፣ ሰላማችንን አጽንተን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ስናረጋግጥ እንዲሁም በኅብር ተናብበን መኖር ስንችል መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም።
በምግብ ራሱን የማይችል ሕዝብና ሀገር ሉዓላዊነቱ በተሟላ ሁኔታ ተረጋግጧል ማለት አይቻልም። ይህ የሚረጋገጠው ሁሉም በተሰማራበት መስክ ተግቶ ሲሰራ ብቻ ነው።
በመሆኑም የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን ለማፅናትና የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር ከፍ ለማድረግ በሁሉም መስክ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዳግም ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት።
“ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፤ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ”