ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል ከነገ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል ከነገ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ ያካሂዳል
ጅግጅጋ ፤ ጥቅምት 3/ 2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ከነገ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤ ኮሚሽኑ ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮች በተከታታይ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በአፋር ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በማሰናዳት ከባለድርሻ አካላቱ የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች ኮሚሽኑ መረከቡን ጠቅሰዋል።
ከነገ ጥቅምት 4/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታተይ ቀናት በሶማሌ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ በሁለት ምዕራፍ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
የክልሉን ስፋት መሰረት በማድረግ በየወረዳው የተመረጡ የማህበረሰብ ወኪሎች የምክክር መድረክ በጅግጅጋ፣ ጎዴ እና ዶሎ አዶ ከተሞች የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም 104 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሦስት በላይ ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአጀንዳ ማሰባሰቡና የምክክር መድረኩ ላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ተሳታፊዎችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና የማህበራት ወኪሎች፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላትና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚገኙ አመልክተዋል።
መድረኩ የክልሉ ባለድርሻ አካላት "መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል" የሚሏቸውን እጅግ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች በህዝባዊ ውይይት የሚሰበስቡበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ የክልሉ ወኪሎች እንደሚመረጡ አስረድተዋል።
መላው የህብረተሰብ ክፍሎችና የባለድርሻ አካላት ተወካዮች በመጪዎቹ ቀናት የሚደረገውን የምክክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ፋይዳ በመረዳት ዝግጅት በማድረግ በንቃት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡