በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የተቋም ግንባታ ሥራዎች የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን የሚያደርጉ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የተቋም ግንባታ ሥራዎች የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን የሚያደርጉ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2017(ኢዜአ)፦ በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የተቋም ግንባታ ሥራዎች የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
"የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት'' በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው ሁለተኛ ዙር የአመራሮች አቅም ግንባታ ሥልጠና ተሳታፊዎች የፌደራል ፖሊስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
በመርኃ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፌደራል ፖሊስ ከሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ እንዲሁም ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ታድመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፌደራል ፖሊስ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚደነቅ ነው።
የፌደራል ፖሊስ የተቋም ግንባታ ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያሳየ መሆኑን በመጠቆም፤ እንደ ከተማ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ማስፋት እና ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በጉብኝቱ የተቋማት ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ለመመልከት መቻላቸውንና፣ ተቋማቱ ትልቅ ውጤት የተገኘባቸውና ተቋማትን ማብቃት እንደሚቻል ያየንባቸው ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።
በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የተቋም ግንባታ ሥራዎች የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
በሁለቱ ተቋማት የተመለከቱት ቴክኖሎጂ ስማርት ሲቲ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከአገራዊ ለውጡ በፊት የፌደራል ፖሊስ አቅም አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከ 2010 ዓ.ም. በኋላ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ መፈጸም በሚያስችለው አቅምና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተቋሙ ራሱን በቴክኖሎጂ በማደራጀት ወቅቱን በዋጀ መልኩ ሽግግር ማድረጉን አስታውቀዋል።
ዛሬ ላይ የፌደራል ፖሊስ ጠንካራ የጸጥታ ተቋም መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን ጠቁመዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ አመራሮች በሥልጠናው ትልቅ አቅም እያገኙ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ጉብኝቱ በቀጣይ ለተቋማት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ባገኙት እውቀት ሕዝባቸውን ለማገልገል እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።