ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ዕድገትና ትስስርን የማሳለጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ዕድገትና ትስስርን የማሳለጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ ቀጣናዊ ዕድገትና ትስስርን የማሳለጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና በአልጀዚራ ጥናት ማዕከል ትብብር "የአፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች፤በዓለም አቀፍ ውድድር ዕድሎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ኃሳብ የተካሄደው መድረክ ተጠናቋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው መድረክ የኢትዮጵያና አፍሪካን ጥቅምና ፍላጎት ለቀሪው ዓለም ማስገንዘብ ያስቻለ ነው ብለዋል።
በመድረኩም የአፍሪካን ሥጋቶች መቀልበስ የሚያስችሉ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መፍትሔ አመላካች ጥናታዊ ጉዳዮች ቀርበው ገንቢ ምክክር እንደተደረገባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሞቿን በማስጠበቅ ለአፍሪካና ቀጣናዊ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነትን ቅድሚያ መስጠት መሆኑን ማስገንዘብ እንደተቻለ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ሠላምና ደኅንነትን በማረጋገጥና ድኅነትን በማሸነፍ በቀጣናዊ ትስስር አብሮ የመልማት ጽኑ ፍላጎት ያላት አገር መሆኗ የተንጸባረቀበት መሆኑም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በምትከተለው በትብብር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የወዳጅነት መርህ የባሕር በር ለማግኘትም ሰላማዊ የመፍትሔ አማራጭ እየተከተለች መሆኑም ተመላክቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ሰላማዊ የመፍትሔ አማራጭ ሰፋ ያለው ማኅበረሰብ ይገነዘባል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤የባሕር በር ጥያቄም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሲሰራበት የቆየ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎትና ዓላማም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በትብብር ላይ በተመሰረተ የልማት ትስስር በመፍጠር ከድኅነት ማላቀቅ መሆኑን የማስገንዘብ ሥራ በስፋት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትም የአትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ማሳየት የሚያስችሉ መፍትሔ አመላካች የጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በማጠናቀቂያ ምዕራፍ የሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በቀጣናው የኃይል ትስስር ማሳለጥ የሚያስችልና በግድቡ ዙሪያ ቀጣይነት ያለው አገራዊ የገጽታ ግንባታ ሥራ እንደሚሰራ አብራርተዋል።