አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በስልጢ ወረዳ ጎፍለላ ቀበሌ የጎርፍ ተፈናቃዮችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በስልጢ ወረዳ ጎፍለላ ቀበሌ የጎርፍ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡

ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቹ በጎፍለላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል::

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ ወቅት፤ ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ ተጎጂዎችን ለማቋቋምና አደጋውን ለመከላከል ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ዘላቂ መፍትሔው ላይ ተጋግዞ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው፤ የተከሰተውን አደጋ ለመከላከልና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከጎርፉ ጋር ተያያዥ የሆኑ የጤና እክሎች እንዳይከሰቱ እንደዞን በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ተፈናቃዮች ክረምቱንና ጎርፉን ተከትሎ ከሚከሰቱ በሽታዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስገንዘባቸውንም የስልጤ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም