ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ያላት ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ያላት ሚና ሊጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ያላት ሚና በቀጣይም ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ በኩዌት ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ እድሪስ ኢብራሂም (ዶ/ር) ገለጹ።
ተመራማሪው እድሪስ ኢብራሂም (ዶ/ር) በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የረዥም ጊዜ ተሳትፎ ያላት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት አሳይታለች ብለዋል።
በሰላም ተልዕኮዎች ውስጥ ያለው ተከታታይ ተሳትፎዋ ለጎረቤቶቿ ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸው፥ይህ የኢትዮጵያ የሰላም ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የጎረቤት አገራትም የኢትዮጵያን የበርካታ ዓመታት የሰላም ማስከበር አስተዋጽዖን ከግምት በማስገባት ያላትን ሚና እንድታጠናክር የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው አንስተዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አገራት እርስ በርስ ተባብረውና ተጋግዘው መሥራት እንዳላባቸው ጠቅሰው፥ በቀጣናው የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለውም ነው ያነሱት።
የቀጣናው አገራት ከታሪካቸው የማያስኬዱ አካሄዶችን በመመርመርና ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለጋራ ሰላምና ልማት የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
ካለፉት ጊዜያቶች ትምህርት ካልወሰድን ያለፉት ጊዜያትን እንደግመዋለን፤በመሆኑም እኛ አፍሪካውያን በራሳችን ጉዳይ ላይ ተወያይተን የራሳችንን መፍትሄ መስጠት አለብንም ብለዋል።