በክልሉ ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ከ6 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር የመፍጠር ተግባር እየተከናወነ ነው

ባህር ዳር፥ ጥቅምት 2/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ከ6 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ፍቅረማርያም የኔአባት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዞቹ ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር የካፒታል አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ ነው።

ከዚህ ውስጥም በበጀት ዓመቱ በ42 ሺህ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 168 ሺህ አንቀሳቃሾች ከ5 ቢሊዮን 954 ሚሊዮን ብር በላይ በሀገር ውስጥ የገበያ ትስስር የመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ባለፉት ሦስት ወራት በተደረገ ጥረት በአራት ሺህ 400 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 17 ሺህ 749 አንቀሳቃሾች 568 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል።

የገበያ ትስስሩ የተፈጠረላቸውም ለከተሞች መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች የሚውል አሸዋ፣ ጠጠርና ብሉኬት እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዲያቀርቡ በማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

የእንጨትና ብረታ ብረት፣ የቢሮ ጥገና፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም ዳቦ ቤቶችን ከምግብ ቤቶች ጋር በማስተሳሰር የገበያ ችግራቸው እንዲቃለል ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

እንዲሁም በ132 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ አንድ ሺህ 320 አንቀሳቃሾች የአንድ ሚሊዮን 430 ሺህ ዶላር የውጭ ሀገር የገበያ ትስስር የሚፈጠር ሲሆን እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ49 ሺህ ዶላር በላይ ትስስር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

የውጭ ሀገር የገበያ ትስስሩም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተላኩ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ውጤቶች መፈጠሩንም አመልክተዋል።

በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የሙሉ ብርቱካን ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ሽርክና ማህበር አመራር ወጣት በረከት አባይ እንዳለው፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ አምስት ሆነው በመደራጀት ስራዎችን በትስስር እያከናወኑ ይገኛል።

በከተማ አስተዳደሩ በዚህ በጀት ዓመት የቢሮ ጥገና ስራ ትስስር ተመቻችቶላቸው እየሰሩ ሲሆን ይህም በአጭር ጊዜ የተሻለ አቅም ፈጥረው ወደ ተቋራጭነት ለማደግ አቅደው እየሰሩ መሆኑንም ተናግሯል።

በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በ27 ሺህ 631 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 110 ሺህ ለሚጠጉ አንቀሳቃሾች ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም