በእንጦጦ ፓርክ የሚገነባው የሰርከስ ማሳያና ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ እየተፋጠነ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2017 (ኢዜአ):- በእንጦጦ ፓርክ የሚገባው የሰርከስ ማሳያና ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ገለጹ። 

ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎች የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ወይዘሮ ሦስና ወጋየሁ በተባሉ ግለሰብ እየተገነባ ያለውን የአፍሪካ ሰርከስ ማሳያና ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ ጎብኝተዋል።

ማዕከሉ በእንጦጦ ፓርክ በ16 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት በግንባታ ላይ ሲሆን በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሏል።

ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአህጉር ደረጃ የሰርከስ ማሳያና ማሠልጠኛ ማዕከል እንደሚሆን ጠቅሰዋል። 

በዚህም ማዕከሉ ለሰርከስ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ኪነ-ጥበብና ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት። 

ማዕከሉ በፍጥናትና ጥራት ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባም በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ድጋፎ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል። 

ወይዘሮ ሦስና መዋለ ነዋያቸውን በኪነጥበብ ዘርፍ ማፍሰሳቸው የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ በኪነ-ጥበብና በስፖርቱ ዘርፍ የባለኃብቶች ተሳትፎ አንስተኛ መሆኑን ገልጸው ባለኃብቶች በዘርፉ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የማዕከሉ ባለቤት ወይዘሮ ሦስና ወጋየሁ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብን ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ የሚሰራ ነው ብለዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ የሰርከስ ጥበብ መዳረሻ ማዕከል የማድረግ ውጥን ያለው መሆኑንም አንስተዋል።

ማዕከሉ የሰርከስ ማሳያ፣ የሰርከስ ጥበብና ዳንስ ማሰልጠኛ፣ ሙዚዬም፣ የወጣቶች ማደሪያና የአሰልጣኞች የሥልጠና፣ ሬስቶራንት ጨምሮ የተለያዩ ክፍሎችን በውስጡ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል። 

ወጣቶችን በአዕምሮና በዕውቀት ለማበልጸግ የሚያስችል የሥልጠና ማዕከል የተካተተበት መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግሥት በኩል መሰረተ ልማት የማሟላትና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም