በአማራ ክልል በ110 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቀድሞ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ

ባህር ዳር፤ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማ መሬት በ110 ሺህ ሄክታር ላይ ቀድሞ የደረሰ ሰብል ከብክነት በፀዳ መልኩ መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ አስላከ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በመኸር ወቅት 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለምቷል።

ቀድሞ የደረሰን ሰብል ለመሰብሰብ በተደረገ እንቅስቃሴም በ110 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ገብስ፣ ቀይ ጤፍ፣ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ እና ሌሎች ሰብሎች ለመሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ አርሶ አደሩ በደቦና የቤተሰቡን ጉልበት አስተባብሮ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የታጨደው ሰብል በዝናብ እንዳይበላሸም በአግባቡ አናፍሶና አድርቆ በመከመር ምርቱን ከብልሽት ሊታደግ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

የሚጥለው ዝናብ በቀሪ እርጥበት ለሚዘሩ ሰብሎች የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፣ አርሶ አደሩ የደረሰን ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ፈጥነው የሚደርሱ የሰብል አይነቶችን መዝራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"የግብርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩ የመሬቱን እርጥበት ተጠቅሞ ተጨማሪ ሰብል ማልማት እንዲችል የቅርብ ድጋፍና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል" ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በምርት ዘመኑ በክልሉ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሰንደቁ ማረው በበኩላቸው እንዳሉት፤ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ሁለት ሄክታር ተኩል መሬተ በገብስ፣ ድንች፣ ስንዴና የጥራጥሬ ሰብሎች አልምተዋል።

በመኸር እርሻ በአንድ ሄክታር መሬት ያለሙትን የገብስና የድንች ምርት ቀድመው ማንሳታቸውን ገልጸው፣ እየጣለ ባለው ዝናብ ለመጠቀምም መሬቱን በስንዴና በሽምብራ እየሸፈኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀድሞ የደረሰን የገብስ ሰብል ምርት አንስተው ቀሪ እርጥበትን ተጠቅመው በዳግም ልማት ገብስ መዝራታቸውን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር ካሳሁን ገደፋው ናቸው።

ወቅቱ ለሰብል ልማት አመቺ በመሆኑ የምግብ ፍጆታቸውን ከማሟላት ባለፈ ተጨማሪ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2015/2016 የምርት ዘመን በክልሉ በተለያዩ ሰብሎች ከለማ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 145 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም