ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገቧ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማ መሆኑን ያሳየ ነው

ጂንካ/ቦንጋ/ሀዋሳ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ሆና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገቧ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እመርታዊ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብትና የታሪክ መምህራን ገለጹ።

ከጂንካ፣ ቦንጋና ሀዋሳ የተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብትና ታሪክ መምህራን እንደገለጹት፤ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማ መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው።

የጂንካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምጣኔ ሀብት መምህር ዳንኤል ታደሰ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ሆና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እመርታዊ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ያመለክታል።

አገሪቷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ዘርፉን ለማዘመን እንዲሁም ያሉትን አቅሞች ለመጠቀም እንደሌማት ትሩፋትና ሌሎች አዳዲስ ዕሳቤዎች በማፍለቅ እያደረገች ያለችው ጥረትንም አድንቀዋል።

ይህም የአገሪቷ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ባለው መልኩ እያሳየ ላለው እድገት እንደምክንያት አንስተው፤ "ማህበረሰቡ በየዘርፉ ለአፈጻጸሙ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር ይኖርበታል" ብለዋል።

ከአገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚው ዕድገት ባሻገር የዜጎችም የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልፀው፤ ለዚህም የዜጎችም ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።

የቱሪዝም የገቢ አማራጭ ተጠቅመው ፈጣን እድገት ያሳዩ አገሮች እንዳሉ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያሏት ሀብቶችና የተፈጥሮ ፀጋዎችን አሟጦ ማልማትና ኢኮኖሚው ላይ የዘርፉን ድርሻ ማጠናከር  እንደሚቻል ገልጸዋል።


 

በቦንጋ ከተማ የቢሻው ወልደዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምጣኔ ሀብት መምህር ተሻለ ፍቃዱ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች የተሰጠው ትኩረት ለኢኮኖሚ እድገቱ መመዝገብ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ኢትዮጵያ ወደ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባቷ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመፍታትና ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት መመዝገብ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚው በላቀ መልኩ ሊያድግ እንደሚችል የተናገሩት መምህር ተሻለ፤ ለዚህ የዜጎች ኋላቀር የስራ ባህል መቀየርና ያሉትን አማራጮች በሙሉ ወደምርት የማስገባት ልምድን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።


 

"ኢኮኖሚን ለማጎልበት ያለንን አማራጭ ሁሉ ወደ ውጤት ለመቀየር መትጋት ይጠበቃል" ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ከተማ የታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር በለጠ ሱጌቦ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በምግብ ሰብል ራስን መቻልና የኢኮኖሚ አቅም መፈርጠም መሰረታዊ ጉዳይ እየሆነ መመጣቱን ጠቅሰው፤ የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ ልማትን ማፋጠንና ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የውሃና መሬት ሀብትን በመጠቀም ኢኮኖሚን ማሻሻል እንደሚቻል ማሳየቱን ጠቁመው፤ እነዚህ ሀብቶችን አቀናጅተን በመጠቀም ለለውጥ መትጋትና መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በተለይም በግብርናው እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ተክቶ ለማምረት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማሳደግም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም