ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ነው

 አዳማ፤  ጥቅምት 02/2017(ኢዜአ)፦ የኢንዱስትሪዎችን  የግብዓት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት ገለፀ ።

የአምራች ኢንዱስትሪ የግብዓት ተግዳሮቶች ላይ የተካሄደን ጥናት በውይይት ለማዳበር ያለመ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ  የሽመቤት ነጋሽ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ተቋሙ ግብዓት የማቅረብ ተልዕኮን በተሻለ ደረጃ ለመፈጸም የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል። 

በተለይም በአሁኑ ወቅት ለኢንዱስትሪዎችና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከአቅም በታች ማምረት ትልቁ ምክንያት የሆነውን የግብዓት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በሚሰራው ሥራ ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ተናግራዋል። 

ድርጅቱ ያሉትን ችግሮች በጥናት መለየቱን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ ይህም ምላሽ የሚያገኘው  የኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት እንዲሁም ምርትና ምርታማነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ስንችል ነው ብለዋል። 

በተለይም የግብዓት አቅርቦት እጥረት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እየተፈታተነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የማምረት አቅማቸውን በዘላቂነት ለማጎልበት ይህ ምክክር አስፈልጓል ነው ያሉት። 


 

የኢትዮጵያ አምራቾች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚሊኬሳ ጃገማ በበኩላቸው የግብዓት እጥረት የአምራች ዘርፉን እየተፈታተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች ውስጥ ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል። 

የአምራች ዘርፉ ያለበትን የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዲሁም የመለዋወጫ፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ተያያዥ ችግሮችን በመፍታት የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

አምራቾች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የግብዓት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ገለፀው፤ ግብዓቶች በግዥ ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎች ተናበው በማምረት የሚፈታ መሆኑን አመልክተዋል። 

መድረኩ የአምራች ዘርፉ ያለበትን የግብዓት አቅርቦት ችግርን በቅንጅት ለመፍታት ቀጣይ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚቀርብበት በመሆኑም ጠቃሚ ሃሳቦች ማመንጨት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ በውይይቱ ላይ በመገኘት ባነሱት ሐሳብ፤ አምራች ድርጅቶች ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን ማሳካት እንዲችሉ ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል። 

የአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በተለይም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የሰው ሃይል፣ መሬትና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሳለጥ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎችን ጭምር በማሻሻል ድጋፍና ዕገዛ እየተደረገ መሆኑን በማንሳት። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም