በአፋር ክልል የእንስሳት ጤና በመጠበቅ ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎል

ሠመራ፤ ጥቅምት 02/2017 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የእንስሳት ሀብት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የእንስሳት እንክብካቤ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር መሐመድ ለኢዜአ እንደገለፁት ለእንስሳቱ ጤና ትኩረት ተሰጥተው ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ ወቅታዊ ክትባት መስጠት ነው።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ገቢ ራሡ ዞን በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች የበሽታ መከላከያ ክትባቱ  ለእንስሳቱ እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

ገዋኔ፣ ገለአሎ፣ ዱለሳ፣ አሚባራ፣ አዋሽ እና አርጎባ ልዩ ወረዳ ደግሞ ለእንስሳቱ ጤና መሻሻል የሚረዱ የህክምና እና የክትባት አገልግሎት እየተሠጠባቸው ካሉት ወረዳዎች መሆናቸውን በማንሳት።

እየተሠጠ ያለው ክትባት የደስታ በሽታ፣የበግና የፍየል ፈንጣጣ በሽታ እንዲሁም የከብቶች የቆዳ መጎረብረብ በሽታ መከላከያ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።


 

በተጨማሪም ለእንስሳቱ በሽታን የመከላከል አቅምን የሚጨምርና የእንስሳት ሞት የሚቀንስ ነው ብለዋል።

ክትባቱ የእንስሳቱን በሽታና ሞትን ከመቀነሱ በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን በማሣደግ ማህበረሰቡ  ከእንስሳቱ ተዋፅኦ በስጋ እና በወተት ምርት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።

የወተትና የስጋ ምርት በማሳደግ የአመጋገብ ሥርዓት ማሻሻል ደግሞ በአገር አቀፍ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውስጥ ከተያዙት ዋና ዋና ግቦች መሆናቸውን በማከል።

በዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ፍየሎች እንዲሁም 300 ሺህ የቀንድ ከብቶች የቆዳ መጉረብረብ መከላከያ ክትባት የሚሰጥ መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፤ በህክምናም ለ36 ሺህ ግመሎች እንዲሁም 120ሺህ በግና ፍየሎች የህክምና አገልግሎት እየተሠጠ ነው ብለዋል።

በሌሎች ቀሪ ወረዳዎችም ጥናት እየተደረገ ክትባቱ የሚቀጥል መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር በሚበዛበት የአፋር ክልል ከ16 ሚሊዮን  በላይ የቤት እንስሳት እንደሚገኙም ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም