በክልሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን በሀገራዊና ክልል አቀፍ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቷል

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 2/2017 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀገራዊና ክልል አቀፍ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን የትምህርት አመራሮች ገለጹ።

የሀላባ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ኤፍሬም ዘለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በሀገራዊና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በ2016 የትምህርት ዘመን የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን አንስተው፣ ይህን ውጤት ዘንድሮ ለመቀየር ከወላጆችና ተማሪዎች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

ለዚህም ትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን እንዲሁም እስከ ወላጅ ድረስ በተሳለጠ መንገድ ሥራዎችን በማከናወን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ስልቶች መነደፋቸውን ተናግረዋል። 


 

የማረቆ ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ሥርጎታ በበኩላቸው እንዳሉት በልዩ ወረዳው በበጀት ዓመቱ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በወረዳው ባለፈው የትምህርት ዘመን በተለይ በሀገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎች የተመዘገበው ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን  ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራዎችን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም መምህራንና ተማሪዎችም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል የሁሉም የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፣ በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን ከመከታተል ባለፈ ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ባለፈው ዓመት በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ እና በ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና የተመዘገበው ውጤት ዝቅተኛ ነው። 

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከመማር ማስተማር ሥራ ጀምሮ እስከ ወላጅ ያለው ክትትልና ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

መማሪያ መጻህፍትን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና መምህራንም ሥራቸውን በተሻለ ብቃት እንዲያከናውኑ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማረቆ ልዩ ወረዳ ቆሼ ከተማ "የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራት" በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም