ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነው ቡናን ለገፅታ ግንባታ እና ዲፕሎማሲ ይበልጥ መጠቀም ይገባል-አምባሳደር ዳባ ደበሌ

አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 2/2017 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ባህል እና ታሪክ መገለጫ የሆነውን ቡና ለገፅታ ግንባታ እና ዲፕሎማሲ ይበልጥ መጠቀም እንደሚያስፈልግ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ገለጹ።

ከመስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በጃፓን ስፔሻሊቲ ቡና ማህበር (SCAJ) አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረው ዓለም አቀፍ የስፔሻሊቲ ቡና አውደ አውደ ርዕይ ዛሬ ተጠናቋል።

በቶኪዮ ‘Big Sight’ በተሰኘው የኤግዚቢሽን ማዕከል በተደረገው የስፔሻሊቲ ቡና አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ አድርጋለች።

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በአውድ ርዕዩ ላይ ተሳትፎ ካደረጉት የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የስራ ኃላፊዎች፣ ቡና አምራቾችና ላኪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የውይይቱ ዓላማ በአውደ ርዕዩ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን እና ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ የኢትዮጵያን ተሳትፎ አጠናክሮ ማስቀጠልን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

አምባሳደር ዳባ፥በአውድ ርዕዩ ላይ ኢትዮጵያ ያደረገችው ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ለተሳታፊዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቡና የኢትዮጵያ ባህል እና ታሪክ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው በተጨማሪ ለገፅታ ግንባታ እና ዲፕሎማሲ ያለውን ሚና ቁልፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው የስፔሻሊቲ ቡና አውድ ርዕይ ኢትዮጵያ ያላትን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአውድ ርዕይ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያን ቡና በቀጣይ በጃፓን ገበያ ይበልጥ በማስተዋወቅ የቡናን ብራንድ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ለዚህም ከመንግስት እና ከሚሲዮን ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በጃፓን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም