የቀጠናው ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስርን ማጠናከርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለጋራ ዕድገት መተባበር ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የቀጠናው ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስርን ማጠናከርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለጋራ ዕድገት መተባበር ይገባቸዋል
ሆሳዕና/ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 2/ 2017 (ኢዜአ)፦ ለቀጠናው ሰላምና ልማት የተፋሰሱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስርን ማጠናከርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለጋራ ዕድገት መተባበር እንደሚገባቸው የዩኒቨርሲቲ የዘርፉ መምህራን ገለጹ።
በጋራ መጠቀም ላይ ያተኮረ ዲፕሎማሲ ከተፈጠረ ለዓለም የሚተርፍ እምቅ የኢኮኖሚ አቅም ቀጠናው ላይ እንዳለ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዋቸሞ እና የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉ መምህራን ገልጸዋል።
የቀጠናው ሀገራት ሀብታቸውን በጋራ የመጠቀምና የትብብር መርህን በማስቀደም ያላቸውን መጻኢ ተስፋ ማራመድ እንደሚገባቸውም ምሁራኑ ተናግረዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት፣ ዓለም አቀፍ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ መምህርና ተመራማሪ አበራ ሄቢሶ እንደገለፁት፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት "የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ታሪክና እሴት ያላቸው ናቸው"።
ሀገራቱ ሰላምን ማስጠበቅና የእርስ በርስ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባቸው አንስተው፤ ቀጠናው ያለው ተፈላጊነት የሚያመጣውን ጫና ወደ ጥቅም ለመቀየር መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በዚህ የቀጠናው ትስስርም የኢትዮጵያ ድርሻ የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን ጨምሮ ያሏትን ሀብቶች ያለማንም ድጋፍ በራሷ አቅም በማልማት ከራሷ አልፋ ለአፍሪካና ለቀጠናው ሀገራት የጋራ እድገት መረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
አያይዘውም የተፋሰሱ አገራት ታላቁ የሕዳሴ ግድብን እንደ ስጋት ሳይሆን የጋራ ሀብት አድርገው መመልከት እንዲችሉ መሥራትም ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህ ላይ ደግሞ እንደ ኢጋድና የአፍሪካ ህብረት ያሉ አህጉራዊ ተቋማትን መጠቀም ትልቅ ውጤት እንዳለው በማከል።
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ትምህርት መምህር ታገል ወንድሙ በበኩሉ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና በርካታ የንግድ ፍሰትና መሰል ጉዳዮች ያሉበትና ዓለም ዓይኑን የጣለበት ወሳኝ ቀጠና መሆኑን ተናግረዋል።
የቀጠናው ሀገራት ለሰላማቸው ሲሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ችግሮችን በውይይት መፍታትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ማስቀደም እንደሚገባቸው በማውሳት።
ሀገራቱ በዲፕሎማሲ የሚመጣውን ሰላም ተጠቅመው ሰጥቶ የመቀበል መርህን ካዳበሩ ለሌላው የሚተርፍ ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠር የሚያስችል ሀብት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በዚህ ቀጠናዊ ትስስርና ዲፕሎማሲ ውስጥ ኢጋድ እና የአፍሪካ ሕብረት ጠንካራ አቋም ይዘው ከውጭ ጣልቃ ገብነት የጸዳ ሰላምና ዕድገትን ለማምጣት የሚያስችል ሥራ በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም መምህራኑ አክለዋል።