ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ሺፕ ማዘጋጀቷ ለስፖርቱ እድገት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/ 2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ሺፕ ማዘጋጀቷ አገሪቱ ለስፖርቱ እድገትና ለአፍሪካ አንድነት ያላት ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሽዊት ሻንካ ገለጹ።  

የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ሺፕ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ነው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በዚሁ ጊዜ፤ ስፖርት ለማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው ሚና የላቀ ነው ብለዋል።  

የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ሺፕ በአህጉሪቱ የሚገኙ አባል አገራት መካከል ያለውን ትስስርና ወዳጅነት ከማጠናከር ባለፈም እንደ አህጉር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላንን ተቀባይነት የሚጨምር መሆኑን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ሺፕ መሥራች ከሆኑት አገራት መካካል አንዷ መሆኗን ገልጸው ኢትዮጵያ ይህንን ውድድር ማዘጋጀቷ ለስፖርቱ እድገትና ለአፍሪካ አንድነት ያላት ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት። 

የአፍሪካ ስፖርት በሁሉም ዘርፍ አድጎ ትስስርን እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ  ረዥም ታሪክ ያላትና ውብና ድንቅ ባህሎች ባለቤት እንደሆነች ጠቅሰው ተሳታፊዎች በቆይታቸው ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹ እሴቶች የሚቀስሙበት አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአፍሪካ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሊድ አልሳይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌስቲቫል እንዲዘጋጅ ላሳየችው ቁርጠኝነት አመስግነዋል። 

ይህ መርኃ ግብር በ2025 በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ማጣሪያነት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ለተወዳዳሪዎችም መልካም ዕድል ተመኝተዋል። 

የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ሺፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ 16 የአፍሪካ አገራት የሚሳተፉበት ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል። 

በውድድሩ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ቶጎ፣ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ ሱዳን፣ ማዳጋስካር፣ ዩጋንዳ፣ ደሞክራቲክ ኮንጎ፣ እና ደቡብ አፍሪካ ይሳተፋሉ።

ውድድሩ በቡድን፣ በነጠላ፣ በጥንድና በድብልቅ በሁለቱም ፆታዎች የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል። 

ለውድድሩም አሸናፊዎች የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም