በክልሉ ወደ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶችና ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ለውጤታማነታቸው በቅንጅት እየሰራን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ወደ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶችና ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ለውጤታማነታቸው በቅንጅት እየሰራን ነው

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 02/2017 (ኢዜአ):- ወደ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶችንና ኢንተርፕራይዞችን ክህሎት በማጎልበትና በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን በሲዳማ ክልል የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ገለጹ፡፡
የክልሉ ስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በበኩሉ ባለፉት ዓመታት የተሰራው በስልጠና የተደገፈ የስራ እድል ፈጠራ የአመለካከት ለውጥ ማምጣቱን ተናግሯል።
በሲዳማ ክልል የሚገኙ 11 የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ወደ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶችን ክህሎት በማጎልበትና ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መልካሙ በራሳ እንደገለጹት ኮሌጁ ላለፉት 25 ዓመታት በመደበኛና አጫጭር ስልጠናዎች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለመፍጠር እየሰራ ነው።
ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ ውጪ ከ14 ሺህ 300 ለሚበልጡ ወጣቶች አጫጭር ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲሰማሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና በቴክኖሎጂ ሽግግር ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ ስራ በመስራት የሚፈጠሩ የስራ እድሎች ክህሎት መር እንዲሆኑ ኮሌጁ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ ዓመትም ከ15 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት በተለይም ለውጭ አገር የሥራ ስምሪት ጭምር ለማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የቀባዶ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ዳንኤል ተሾመ በበኩላቸው ኮሌጁ እንደአገር የተያዙ አዳዲስ እሳቤዎችን ተግባራዊ የማድረግ ተልእኮውን ለመወጣት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ብቁ፣ ተወዳዳሪና በገበያ ተፈላጊ ሰልጣኞችን ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ በ2016 ዓ.ም ከመደበኛ ስልጠና በተጨማሪ ከ1 ሺህ 600 ለሚበልጡ ሰልጣኞች ገበያ ተኮር አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠትም የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ገዛኸኝ ወልደሰንበት በበኩላቸው ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ ስኬታማነት ግብ ተፈራርመው ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በኮሌጁ ከመደበኛ ስልጠና ባሻገር በአጫጭር የስልጠና ፕሮግራም ገበያ ተኮር ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራት የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከ13 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በማሰልጠን ብቁና ተወዳዳሪ ከማድረግ ባሻገር ኃብት እንዲያፈሩ የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
ለነባርና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር በሰሩት ስራ እውቅና ማግኘታቸውን በማከል።
የሲዳማ ክልል የስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ የስራ እድል ፈጠራ ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት 15 ወራት ከ78 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች ገበያ ተኮር አጫጭር ስልጠናዎችን በማሰልጠን ወደ ስራ ማሰማራት እንደተቻለ ተናግረዋል።
በክልሉ ካሉ ቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተሰራው በስልጠና የተደገፈ የስራ እድል ፈጠራ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ጭምር ማስቻሉን ነው የተናገሩት።
የሲዳማ ክልል የስራ ክህሎትና ኢንተርፕይዞች ልማት ቢሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና በየደረጃው ያሉ የመንግስት የአመራር አባላት በተገኙበት የ2017 የዘርፉን ጉባዔ ማካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።