አቶ አደም ፋራህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ አደም ፋራህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል የሆነውን የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።
አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተገነቡ የሚገኙ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል የሆነው የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ ያለበትን ደረጃ በዛሬው እለት ጎብኝተናል ብለዋል።
ከጅግጅጋ 25 ኪሜ ርቀት ላይ በፋፈን ዞን ሸቤልለይ ወረዳ የተጀመረው የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ 10 ወራት ያስቆጠረ ሲሆን በውስጡ ለቱሪስት መስህብ የሚያገለግሉ 8 ዘመናዊ መንደሮች፣ 3 ሰው ሰራሽ ግድቦች፣ ለመንደሩ የሚያገለግል 13 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት ግንባታ፣ የውሃ፣ የመብራት እና የቴሌኮም ሙሉ መሰረተ ልማት ተሟልቶለታል።
ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድልን እንዲሁም ለከተማው መነቃቃትን ከመፍጠሩም በላይ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር ታስቦ በመገንባቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ለጎረቤት ሀገራት ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ እንደሚሆንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጠር አምናለሁ ብለዋል።
በተለይም ከበርበራ እስከ ውጫሌ፣ ከጅግጅጋ እስከ ጅቡቲ በመሰራት ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ከሸቤልለይ ሪዞርት ጋር ተጣምረው ጅግጅጋ ከተማን ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚያደርጓት ይጠበቃል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን እየሰሩ ያሉ የፌዴራልና የክልሉን አመራሮች እንዲሁም ተቋራጭ ድርጅቶችን እያመሰገንኩ ፕሮጀክቱ ከፍፃሜ እንዲደርስ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ እላለሁ ሲሉም አስፍረዋል።