የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ 16 የአፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መካሄድ ጀመረ።
ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።
በውድድሩ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ቶጎ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ ሱዳን፣ ማዳጋስካር፣ ዩጋንዳ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ እና ደቡብ አፍሪካ ተሳታፊዎች ሆነዋል።
አገራቱ ለዚህ ውድድር የበቁት በአምስት ምድብ ተከፍለው የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ማጣሪያ ውድድር ከተደረገ በኋላ የየምድቡ አሸናፊዎች በመሆናቸው ነው።
በዚህም መሰረት ውድድሩ በአራት ዓይነት ዘርፎች በቡድን፣ በነጠላ፣ በጥንድና በድብልቅ በሁለቱም ፆታዎች የሚካሔድ ይሆናል።
ለውድድሩም አሸናፊዎች የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል።
በሻምፒዮናው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የአፍሪካ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሊድ አልሳይ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሽብር ወልደጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ብዛኔ እና ሌሎችም ታዳሚዎች ተገኝተዋል።