ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተወሰደ ላለው የሕግ ማስከበር ሥራ ስኬታማነት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን 

መተማ፤ ጥቅምት 2/2017 (ኢዜአ):-  በምዕራብ ጎንደር ዞን የጥፋት ኃይሎችን አጀንዳ ካለመቀበል ባለፈ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተወሰደ ላለው የህግ ማስከበር ሥራ ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የገንዳ ውሃ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

''በአማራ ክልል ወጣቶች ከመንግስት ጎን ሆነው ለክልሉ ሰላምና አንድነት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል'' ሲሉ የክልሉ አድማ መከላከል ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አበበ ውቤ ገልፀዋል። 

በገንዳ ውኃ ከተማ በወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ላይ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ውይይት ተካሄዷል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት አምላኩ ይሁን እንዳለው፤ በፀጥታ ችግር ምክንያት በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው መንገላታትና የልማት መስተጓጎል በጠንካራ የህግ ማስከበር ሥራ ማስቆም ይገባል።

ግጭትን ከሚያባብሱ ጉዳዮች በመራቅና ለፀጥታ አካላት ተገቢውን መረጃ በመስጠት ለዘላቂ ሰላም መስፈን እየተከናወነ ባለው የህግ ማስከበር ስራ ውጤታማነት የድርሻውን እንደሚወጣም ተናግሯል።

አካባቢው በቂ ሀብት ያለው ቢሆንም በተደጋጋሚ በሚከሰት የሰላም እጦት በተፈለገው መጠን ለምቶ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የገለጸው ደግሞ ወጣት አዲሱ ነጋ ነው።

"ካለፈው ልንማር ይገባል" ያለው ወጣቱ ለዘላቂ ሰላም እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ስራ በአንድነት መደገፍና ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ተናግሯል።


 

ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት መታደል መልካሙ በበኩሏ፤ "ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በአካባቢው ያለውን የሰላም ችግር ማቃለል የሁሉም ወጣት ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል" ስትል ተናግራለች።

"የጥምር ፀጥታ አካላት ከወጣቱ ጋር ለመስራት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው" ያለችው ወጣቷ፤ ሰላም ከሌለ የሚፈጠር የስራ እድልም ሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደማይኖር በተግባር አይተነዋል በማለት ገልጻለች።

በተደራጀ መንገድ ሰላምን ማረጋገጥ ግዴታ እንደሆነም ወጣት መታደል ገልፃለች።

በፀጥታ ችግር ህብረተሰቡም ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረገ በመሆኑ የሰላም አማራጭን መከተል ተገቢ መሆኑን የገለፀው ደግሞ ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት አሸናፊ ተፈራ ነው።

የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት የጀመራቸውን ሥራዎች ከዳር ለማድረስ ሰላም ወሳኝ መሆኑን የጠቀሰው ወጣቱ፣ ለአካባቢያቸው ሰላም ከፀጥታ አካሉ ጎን ሆኖ እንደሚሰራ አረጋግጧል።

የክልሉ አድማ መከላከል ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አበበ ውቤ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የክልሉ ወጣቶች ለጥፋት ሀይሎች መጠቀሚያ ሳይሆኑ ከመንግስት ጎን ሆነው ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል። 

በዓላማ የፀና፣ ህግን አክብሮ የሚያስከብር ትጉህና ታታሪ ወጣት መገንባትና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ወጣቶች ለጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ሳይሆኑ ከመንግስት ጎን ሆነው በመንቀሳቀስ የህዝብ አለኝታነታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በተለይ ለሰላምና አንድነት ጠንክረው በመስራት በአገር ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በአገር መከላከያ ሠራዊት የ504ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል ኤርቄሎ ዱካቶ በበኩላቸው፤ የተጀመሩ የመልካም አስተዳደርና የልማት ሥራዎችን ለማጠናከርና ሰላምን ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የወጣቱ ድርሻ የላቀ ነው።

ወጣቶች ለሀገር አንድነትና ለህዝቦች ሰላም የቆመ የፀጥታ ሀይልን በመደገፍ፣ ህግና ስርዓት እንዲከበርና አካባቢያቸው ሰላም እንዲሆን አበክረው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"በህዝብ ስም በመነገድ ልማትን ማደናቀፍና የራስን ኪስ መሙላት ሊቆም ይገባል" ሲሉም ብርጋዴል ጄነራል ኤርቄሎ ገልፀዋል።

የገንዳ ውሃ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሃመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ወጣቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የፀጥታ አካሉን መደገፍ አለባቸው።

"ከተማዋ አሁን ላለችበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የወጣቱ ሚና የላቀ ነው" ያሉት አቶ አብዱልከሪም፣ በቀጣይም የከተማዋን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ወጣቱ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በከተማዋ ያሉ ፀጋዎችን ለይቶ ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም