የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎቶችን እንድናዳብር ረድቶናል

አዳማ ፤ ጥቅምት 02/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና ለችግሮች መፍትሔ  የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ሀሳቦችንና ክህሎቶችን ለማዳበር እንደረዳቸው  የኢትዮጵያን ኮደርስ ሰልጣኝ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ  ዩኒቨርሲቲ ልዩ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ናታኔም አበራ የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና "ከዓለም እኩል መራመድ እንድንችል የሚያግዘን እውቀት ያገኘንበት ስልጠና ነው" ብሏል፡፡

የኮደርስ ስልጠናው የተለያዩ የፕሮግራሚንግ ቋንቋዎችንና ዌብሳይት አሰራር ዕውቀት የቀሰሙበት ወርቃማ የትምህርት እድል እንደሆነ በማከል፡፡   

ከስልጠናው ባሻገር "የብቃት ማረጋገጫ ፈተናና የእውቅና የምስክር ወረቀት ያለው መሆኑ ደግሞ ፋይዳውን ከፍ ያደርገዋል" በማለት ነው የገለጸው፡፡

"ስልጠናው እንደ መልካም አጋጣሚ የተገኘ እድል ነው" የሚለው ታዳጊ ናታኔም፤ ዓለም አቀፍ እይታን ማዳበር የሚያስችለን  ነው ብሏል።

በስልጠናው የተገኘውን እውቀት መሰረት አድርጎ ራሱን በማብቃት በየስራ ዘርፉ፣ በልማትና በሀገር እድገት ላይ እንቅፋት ለሆኑ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርግም ምኞቱን ገልጿል፡፡

ሌላዋ የስልጠናው ተሳታፊና የብቃት የምስክር ወረቀት ያገኘችው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ፌኔት ገነነ ነች፡፡


 

ተማሪ ፌኔትም በአዳማ ሳይንስና ቴንክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና መውሰዷ እየተከታተለችው ላለው የሳይበር ስልጠና የእውቀት ግብዓት ሆኖ እንዳገለገላት ተናግራለች፡፡ 

የተለያዩ "የፕሮግራሚንግ ስራዎችን በቀላሉ መስራት እንድችል ረድቶኛል" ስትልም ገልጻለች፡፡

በማሽንና ሰው ሰራሽ ልህቀት ትምህርቶች መሰረታዊውን የቴክኖሎጂ ክህሎት መያዝ  ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ጠቁማ፤ በዲጂታሉ ዓለም ተግባራት በቀላሉ ለመተግበር ሊኖራቸው የሚገባ ቁልፍ መሆኑን ገልጻለች፡፡


 

ተማሪ ፍቅር ዓለምም እንዲሁ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ትምህርት ቤት 11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡

ታዳጊው የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና አጠናቆ የምስክር ወረቀት ማግኘት የቻለ ነው፡፡ በስልጠናው "የችግር አፈታት መሰረታዊ ክህሎት አግኝቼበታለሁ" ይላል፡፡

በስጠናው በመታገዝ  ስለ ጃቫ ስክሪፕት ማወቅና የተለያዩ ዌብሳይቶችን ዲዛይን ማድረግ መቻላቸውንም ይጠቅሳል፡፡


 

በአዳማ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሪሶ ዶሪ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና ከወሰዱት መካከል 26 የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስልጠናውን በሚገባ አጠናቀው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም