ኢትዮጵያ እና ማላዊ በፍልሰተኞች መብት አጠባበቅ፣ የሕግ እና የወንጀል ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ማላዊ በፍልሰተኞች መብት አጠባበቅ፣ የሕግ እና የወንጀል ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ማላዊ በፍልሰተኞች መብት አጠባበቅ፣ የሕግ እና የወንጀል ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ አስታወቁ።
የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ከማላዊ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ዶክተር ኬን ዚካሌ ንጎማ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሁለቱ አገራት በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን በጋራ መከላከልና መቆጣጠር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
በደቡብ የፍልሰት መስመር ከኢትዮጵያ ማዕከላዊና ደቡባዊ አካባቢዎች በመነሳት ኬንያን፣ ታንዜኒያን፣ ማላዊን፣ ዛምቢያንና ሞዛምቢክን በማቋረጥ እስከ ደቡብ አፍሪካ በተዘረጋው የሰው አዘዋዋሪዎች የወንጀል መረብ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ አገራቸውን ለቀው እንደሚፈልሱ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በሰው ነጋዴዎችና ድንበር አሻጋሪዎች አማካኝነት ለከፍተኛ ስቃይና ብዝበዛ እንዲሁም ለሞት እንደሚዳረጉ አመልክተዋል።
የማላዊ ሕዝብና መንግስት በግዛታቸው የተገኙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ከአዘዋዋሪዎች እጅ በማዳንና በአገራቸው በማቆየት እያሳዩ ላለው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
የማላዊ መንግስት የሰው አዘዋዋሪዎችንና ድንበር አሻጋሪዎችን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ እየወሰደ ያለውን እርምጃ የኢትዮጵያ መንግስት ያደንቃል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር በፍልሰተኞች መብት አጠባበቅ፣ የሕግ እና የወንጀል ጉዳዮች ላይ በትብብር የመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል።
የማላዊ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ዶክተር ኬን ዚካሌ ንጎማ ማላዊ እና ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ከመንግስታቸው ጋር ተባብሮ ለመስራት ያቀረበውን ጥያቄ እንደምትቀበለው አመልክተዋል።
ማላዊ ወንጀሎቹን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በአገራቱ መካከል መደበኛ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
ይህንንም እውን ለማድረግ የፍትሕ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከሚገኘው የማላዊ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እንዲሰራ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።