ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 8 ሶስተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከጊኒ ጋር ታከናውናለች።
የሁለቱ አገራት ጨዋታ ኮትዲቭዋር በሚገኘው ኢቢምፔ ኦሊምፒክ ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 8 እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 0 ሲሸነፍ፣ ከታንዛንያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል።
ውጤቶቹንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በ49 ዓመቱ የጊኒ እና ፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ባለው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ቻርልስ ፓኩዌሌ የሚመራው የጊኒ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በታንዛንያ 2 1 ለ እንዲሁም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 1 ለ 0 ተሸንፏል።
ጊኒ ያለ ምንም ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ አራተኛ ደረጃ ይዛለች።
ዋልያዎቹ ዛሬ ከጊኒ ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በሊሴ ሞደርን ዲ'ኮኮዲ ሜዳ ማከናወናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
22 ተጫዋቾች ልምምድ ያከናወኑ ሲሆን አጥቂው ቢንያም በላይ ከጉዳት ባለማገገሙ በልምምዱ ላይ አለመሳተፉ ታውቋል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በማጣሪያው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
የ36 ዓመቱ ኮትዲቯራዊ ክሌመንት ፍራንክሊን ፓን የሁለቱ አገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ኢትዮጵያ እና ጊኒ የምድብ አራተኛ ጨዋታቸውን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በኢቢምፔ ኦሊምፒክ ስታዲየም ያደርጋሉ።
ዋልያዎቹ ከኦዞዎቹ ጋር የሚያደርጓቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች በአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፋቸውን ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅም አላቸው።
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 8 ከትናንት በስቲያ በተደረገ ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታንዛንያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ውጤቱን ተከትሎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነጥቧን ወደ ዘጠኝ ከፍ በማድረግ የምድብ መሪነቷን አጠናክራለች።
ታንዛንያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።