በኢንቨስትመንት ዘርፍ የቻይና ባለሃብቶች በ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መዋለ ንዋይ ስራ ላይ አውለዋል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በኢንቨስትመንት ዘርፍ የቻይና ባለሃብቶች በ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መዋለ ንዋይ ስራ ላይ አውለዋል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የቻይና ባለሃብቶች በ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መዋለ ንዋይ ስራ ላይ በማዋል በሀገር ዕድገት ላይ ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
በ2017 የመጀመሪያው ሩብ በጀት ዓመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍስት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ12 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ እንደተቻለም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በዱከም የኢስተርን ኢንዳስትሪ ዞን ጉብኝት አድርገዋል።
በኢንዱስትሪ ዞኑ በኢንቨስትመንት ከተሰማሩት መካከል የሊንዳ ኢትዮጵያ ጋርመንት፣ ሁዋጃ አሉሙኒየምና ዲ ዋን ሴራሚክስ የተሰኙ የቻይና ኩባንያዎች ተጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርግ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግም በፌደራልና በክልል መንግስት እንዲሁም በቻይና ባለሃብቶች የተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሟላ የመሰረተ ልማት ማሟላት እንደተቻለ ተናግረዋል።
ጉብኝት የተደረገበት የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክም 153 የውጭ ባለሃብቶች የሚያለሙበትን ዕድል በመፍጠር በኢትየጵያ ካሉ ተቀዳሚው ግዙፍ የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ መካከል መሆኑን አብራርተዋል።
በፓርኩም 93 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ የቻይና አልሚ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች እያለሙ የሚገኝ ሲሆን ቀሪውን ደግሞ የህንድና የእንግሊዝ አልሚዎች መሸፈናቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ የቻይና ፕሮጀክቶች በ8 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል ብለዋል።
የቻይና ኩባንያዎችም በተኪ ምርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በንግድ ትስስር በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከ325 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቢ፤ የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ላይ የሚጋጥማቸውን ችግር መፍትሔ ለመስጠት ቀጣይነት ያለው የመስክ ምልከታ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ የገቢና ወጪ ምርት የንግድ ዘርፎች ክፍት በመደረጋቸውም የውጭ ባለሃብቶች የተሳትፎ ፍላጎት ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተዘግተው የነበሩ የገበያ አማራጮችን ክፍት በማድረግ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ድጋፍ በማድረግ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚቀርቡ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠት ገንቢ ሚና እየተጫዎተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተለያዩ መስኮች ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር አጠቃላይ የ12 በመቶ የኢንቨስትመንት ፍስት ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል።
በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የተሰማሩ ቻይና ባለሃብቶችም በሚደረግላቸው የቅርብ ድጋፍ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።