በታማኝነት ግብር መክፈል ለሀገር መታመን በመሆኑ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የምናደርገው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ታማኝ ግብር ከፋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በታማኝነት ግብር መክፈል ለሀገር መታመን በመሆኑ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የምናደርገው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ታማኝ ግብር ከፋዮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦በታማኝነት ግብር መክፈል ለሀገር መታመን በመሆኑ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የምናደርገው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
የስድስተኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በትናንትናው እለት መካሄዱ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ሁነት ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ ግብር ከፋዮች የዜግነት ግዴታችሁን ለመወጣት ላደረጋችሁት ቁርጠኝነት ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
ለታማኝነታችሁ መንግስት የከፈላችሁት ግብር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተሸላሚ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ግብር ከፋዮች ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ መክፈል አገርን የመውደድ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው ለተሰጣቸው እውቅናም አመስግነዋል።
በታማኝነት ግብር በመክፈል በተከታታይ ዓመታት የፕላቲኒየም ተሸላሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፤ ግብር መክፈል የልማት፣ የአንድነት፣ የሰላም አጠቃላይ የሀገር እድገት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ንግድ ባንክ በታማኝ ግብር ከፋይነቱ ለሀገር እድገት እየሰራ መሆኑን ጠቅስው በዚሁ ስራ ለተሰጠው እውቅናም አመስግነዋል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል የኃይሌና አለም ድርጅት ተወካይ የሆኑት አለም ጥላሁን፤ ለተሰጣቸው እውቅና አመስግነው በታማኝነት ግብር የመክፈል ጉዳይ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በታማኝነት ግብር መክፈል ለሀገር መታመን በመሆኑ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የምናደርገው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የናሽናል ኦይል ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ታደሰ ጥላሁን፤ ሁሉም በተሰማራበት ተግቶ በመስራትና የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ በመክፈል ለሀገር እድገት መስራት ግደታ መሆኑን አንስተዋል።
ግብርን መሰወርና በወቅቱ አለመክፈል በሀገር ላይ ወንጀል መፈፀም በመሆኑ ታማኝነትን በተግባር ማሳየት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በሀዋሳ ኢንዱሰትሪ ፓርክ በጨርጨርቅ ኢንዱስትሪ ምርት ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ኢንዱጅን ድርጅት ተወካይ ላሳንታ ሳምራሊኔ የኢትዮጵያ መንግስት ለኢንቨስትመንት ከሚሰጥ ማበረታቻ በተጨማሪ ለከፈሉት ግብር እውቅና መስጠቱ አመስግነዋል።
በወተት ምርት ላይ የተሰማራው ቺዘር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተወካይ ዳዊት እሸቱ፤ ለሀገር ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ግብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ለታክስ ህግ ተገዥ በመሆን ግብርን በታማኝነት መክፈል የሀገር ውለታና ግደታም ጭምር በመሆኑ ሁላችንም ግደታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
የእውቅና መርሃ ግብሩ የታክስ ህግ ተገዥነትን በማበረታታት ግብርን በታማኝነት መክፈልን የሚያበረታታ መሆኑ ይታወቃል።