የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና መከታተል ይገባል- ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዓቢይ ኮሚቴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና መከታተል እንደሚገባ ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዓቢይ ኮሚቴ አሳሰበ።

ዓቢይ ኮሚቴው የ2016 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አፈፃፀምና የ2017 በጀት ዓመት መነሻ ዕቅድን ገምግሟል።

የ2016 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አፈፃፀም ጥሩ ውጤት የታየበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የችግኝ ተከላ ወቅት ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራን በሳይንሳዊ መንገድ በመደገፍ ያመጣውን ለውጥ ማጠናከር፣ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማዘመንና የክልሎችን አቅም ማሳደግ ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

በ2017 በጀት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የችግኝ ተከላ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ የተከላ ቦታ ልየታና የካርታ ዝግጅት ለመስራት በዕቅድ መያዙም ተገልጿል።

በ2016 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ “የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉ ተጠቁሟል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉንና እስከ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚተከለውን ችግኝ ወደ 50 ቢሊዮን ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም