ቀጥታ፡

የአዘርባጃን የንግድ ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦የአዘርባጃን የንግድ ልዑካን ቡድን የግብርና ኢንቨስትመንት እድሎች እና አማራጮች ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተገለጸ።

ጉብኝቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የግብርና ኤክስፖርት ትብብር ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሩሲላን ናሲቦቭ ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

ሚኒስትሩ ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛው ዘርፍ መሆኑንና ይህን ወሳኝ ዘርፍ ወደ ተሻለ ምርታማነት ለማሸጋገር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ዘርፍ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስና ለማስተካከል እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በመተግበር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ጠቁመዋል።

የተተከሉ ችግኞች የፍራፍሬ፣ የደን፣ ቡና እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በምግብ ራስን ለመቻል ከተሰሩ ስራዎች መካከል የመስኖ ስንዴ ልማት እንደሚገኝበት የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በስንዴ ምርታማነት ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ነው የተናገሩት።

ግብርናውን ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመጠቆም።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ግብርና፣ የመሬት ምዝገባና አጠቃቀምን ማዘመን፣ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርትና ሌሎችንም ተሞክሮዎች ከአዘርባጃን ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና ኢንቨስትመንት አቅም ያላት ሲሆን የአዘርባጃን ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሩሲላን ናሲቦቭ በበኩላቸው አገራቸው በውሃ ማቆርና አጠቃቀም፣በዲጂታል ግብርና፣ እንዲሁም በግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ሰፊ ልምድና ውጤታማ ተሞክሮ እንዳላት ገልጸዋል።

አገራቸው በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የግብርና ኢንቨስትመንት በመጠቀም በዘርፉ ለመሰማራት የአዘርባጃን ባለሀብቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

የአዘርባጃን የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።

ጉብኝቱ ከኢንቨስትመንቱ በተጨማሪ በሁለቱ አገሮች መካከል የግብርና ኤክስፖርት ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያስችል አምባሳደሩ መግለጻቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም