የኢትዮጵያ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ጨዋታ በብሩንዲ ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ጨዋታ በብሩንዲ ተሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከብሩንዲ አቻው ጋር ባደረገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ 3 ለ 2 ተሸንፏል።
በአዛም ኮምሌክስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ክሪስቶፍ ንዳይኬንጉሩኪዬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ዴስቲን ማኒሪሆ ቀሪዋን ጎል ለብሩንዲ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
አንተነህ ተፈራ እና ሚኪያስ ፀጋዬ ለኢትዮጵያ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ውጤቱን ተከትሎ በምድብ 2 የምትገኘው በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
ተጋጣሚዋ ብሩንዲ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
በዚሁ ምድብ በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
ዩጋንዳ ከምድቡ ሰባት ነጥብ በማግኘት አንደኛ ደረጃን ይዛ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፋለች።
በማጣሪያው በምድብ 2 ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ተደልድለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
ታንዛንያ እና ሱዳን በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኬንያ በ4 ነጥብ፣ ሩዋንዳ በ1 ነጥብ እና ጅቡቲ ያለ ምንም ነጥብ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በዚህ ምድብ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉ አገራትን የሚለዩ የምድብ ጨዋታዎች ጥቅምት 3 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄዱ ሴካፋ አስታውቋል።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በውድድሩ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
እ.አ.አ በ2025 በሚካሄደው 24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።