ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ወሳኝ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከሳይበር ጥቃት በመጠበቅ ሉዓላዊና ጠንካራ ሀገር መገንባት ይገባል- አቶ ማሞ ምህረቱ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ወሳኝ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከሳይበር ጥቃት በመጠበቅ ሉዓላዊና ጠንካራ ሀገር መገንባት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ። 

የዲጂታል ስርዓቱን ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ ለማድረግ ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡  

ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር "የቁልፍ መሠረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር በሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል። 

የሳይበር ደህንነት ወር እንደ ሀገር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እየተካሄደ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ21ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው። 

የሳይበር ደህንነት ወር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን በማከናወን የሚካሄድ መሆኑ ተጠቁሟል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ የኢትዮጵያን ወሳኝ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከሳይበር ጥቃት በመጠበቅ ሉዓላዊና ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የሀገር ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሳይበር ደህንነት ቁልፍና ወቅታዊ ጉዳይ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የዲጂታል ሃብቶችን የመጠበቅ እና የዜጎችን ደህንነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ ለሳይበር ደህንነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ስርዓት ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው ይህንን የተሟላ ለማድርግ የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በሳይበር ቴክኖሎጂ ልማት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት በማገዝ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ማበልጸግ ይገባልም ነው ያሉት። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዕቅድ መሠረት የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ቁልፍ መሠረት ልማቶች ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገቶች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቁመው ተቋማቸው በከፍተኛ ትኩረት ከሳይበር ጥቃት በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ 

የሳይበር ደህንነት ወር መከበርም የዜጎችን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር የላቀ ፋይዳ እንዳለው አንስተው በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ ከቢሊዮን ብር ኪሣራ መታደግ መቻሉንም አስታውሰዋል።  

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ፤ የሀገርን መሠረት ልማቶች ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡


 

የመሠረተ ልማት ጥበቃዎች በተጻፉ ህጎች ብቻ ሳይሆን በጥሩ ልምምድና ተሞክሮ ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ከ23 ሺህ ኪሎ-ሜትር በላይ የፋይበር መስመርና ከ8 ሺህ 500 በላይ የሞባይል ጣቢያዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ሁሉም ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ኩባንያው የዘረጋውን መሠረት ልማት ተጠቅመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። 

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሌሎችም እንግዶች ታድመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም