የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭ ሥልጠና አገር በቀል የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ለማስፋት ያግዛል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭ ሥልጠና  አገር በቀል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ለማስፋትና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን መሰረት እንደሚጥል  ተገለጸ።  

"5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ" ሥልጠና አገር በቀል መፍትሔዎችን የሚሰጡ ወጣቶችን ለማፍራት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር)  ይፋ የተደረገ ኢንሼቲቭ ነው።

የጎግል ኩባንያ የፓን አፍሪካ ተቋማት ኃላፊ ፕሬንሲልያ ቦኣጉሄ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር እያከናወነች ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ  ችሎታ ያላቸው ወጣቶችን ለማፍራት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ነው ያነሱት።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ የስቲም ፓወር ማዕከላት ለማትስ፣ ኢንጅነሪንግና ሳይንስ ትምህርቶች ትኩረት በመስጠት ፈጠራን ለማበረታታት የጀመረችው ተግባር በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል። 

በተለይም "5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ" ሥልጠና በግብርና፣ ጤና፣ ትራንስፖርት፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ እንደሚያስችልም ገልጸዋል። 

አገሪቱ እያከናወነች ላለው ምጣኔ ኃብት እድገት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአገር በቀል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች መፍትሄ ለመስጠት መሰረት እንደሚጥልም ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብና ወጣት የሰው ኃይል ብዛት አንጻር ታዳጊዎች ላይ መሥራት የአህጉሪቱን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያፈልቁ ወጣቶችን ለማፍራት ይረዳል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር ለማስፋት የጀመረችውን ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ይህም እውን ለማድረግ ጎግል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

አፍሪካውያን ተማሪዎችን በኮምፒውተር ሳይንስ፣ ሮቦት እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ክህሎትና እውቀታቸውን ለማዳበር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም