ባለፉት ሦስት ወራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አበረታች እድገት አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሦስት ወራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አበረታች እድገት አስመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 የመጀመሪያው ሩብ በጀት ዓመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ12 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
ከ3 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ከ8 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ የሚገኘውን የኢስተርን ኢንደስትሪ ፓርክ ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱም በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩት 153 በላይ የውጭ አልሚ ባለኃብቶች መካከል የቻይና ኩባንያዎች የሆኑት የሊንዳ ኢትዮጵያ ጋርመንት፣ ሁዋጃ አሉሙኒየምና ዲ ዋን ሴራሚክስ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበር ኩባንያዎች ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያን ለአገር ውስጥና ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አልሚ ባለኃብቶች ተመራጭ ማድረግ ያስቻሉ የአዋጅና የአሰራር ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ መዋለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ ላይ ከሚገኙ 153 የውጭ ባለኃብቶች ውስጥ 93 ከመቶ የቻይና ባለኃብቶች ሲሆኑ ቀሪው ደግሞ የህንድና የእንግሊዝ ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ አጠቃላይ ከ3 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ከ8 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ በሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
እነዚሁ የቻይና ኩባንያዎችም በተኪ ምርት፣ በክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርና በንግድ ትስስር እያበረከቱት ከሚገኘው አስተዋጽኦ ባሻገር ከ325 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችን ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል ብለዋል።
በተለይም በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ገንቢ ሚና በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያላት ዕምቅ የመልማት አቅም ከቀጣናው አገራት ባለፈ የአፍሪካ አህጉር ተቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻና ተመራጭ እንድትሆን እያስቻላት እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዚህም በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ግብርና፣ አይሲቲና ቱሪዝም መስኮች ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ12 ከመቶ የኢንቨስትመንት ፍስት ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቢ፤ ኮሚሽኑ የአገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት የሚያስችል የድጋፍና ክትትል ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚክና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማድረግ ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንደተቻለም ገልጸዋል።
በዚህም ወደ ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚመጡ አልሚዎች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አብራርተዋል።