ቀጥታ ስርጭት

የኮምቦልቻ ከተማን በኮሪደር ልማት ለማስዋብና ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው--ከንቲባው

ደሴ ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ የኮምቦልቻ ከተማን የኮሪደር ልማት በማስፋት ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለኢንቨስመንት ምቹ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ የከተማው ከንቲባ አስታወቁ።  

የከተማው ከንቲባ አቶ መሀመድ አሚን የሱፍ እንደገለጹት፤ ከተማውን በኮሪደር ልማት በማስዋብ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለኢንቨስመንት ደግሞ ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡


 

ባለፈው ዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድን ጨምሮ የእግረኛና የአካል ጉዳተኞች መንገድ፣ መዝናኛ፣ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች መሰረተ ልማት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም የኮሪደር ልማት ጅምሩን በማጠናከርና በማስፋት ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የኮሪደር ልማቶችን ለማከናወን የዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

በልማቱ የቆሻሻ መጣያ አካባቢዎችንና የወንዝ ዳርቻዎችን የማጽዳትና የማልማት ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰው፤ ከሌሎች ከተሞች ልምድ በመውሰድ የተሻለ ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል፡፡

ለስራው መሳካትም ህብረተሰቡን፣ ባለሃብቱንና ተቋማትን ጭምር በማስተባበር የሚሰራ ሲሆን፤ በዚህም በየአካባቢው የመንገድ አካፋዮችን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን በማልማት እንዲደግፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ አቶ አወል ሰይድ በበኩላቸው፤ ከተማዋን በኮሪደር ልማት ለማስዋብ የተጀመሩ የልማት ስራዎች አበረታች ናቸው።


 

ለውጤታማነቱም በሚችሉት አቅም ሁሉ ለማገዝና ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ባለፈው በጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚልቅ በጀት የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የተገነቡ መሰረተ ልማት ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም