ቀጥታ፡

ከ300 በላይ የመንግስት ጤና ተቋማትን በታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የሙከራ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

በኢትዮጵያ በተመረጡ ከ300 በላይ የመንግስት ጤና ተቋማትን በታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የሙከራ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ። 

በኢትዮጵያ ከ300 በላይ የመንግስት ጤና ተቋማትን በፀሀይ የሚሰራ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎችን  የሚያስጠቅም የሙከራ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ። 

ፕሮጀክቱ በጤና ሚኒስቴር፣ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና በአለም አቀፉ የክትባት ጥምረት (ጋቪ) አጋርነት የሚተገበር ነው ተብሏል። 

ፕሮጀክቱ ከዋናው ግሪድ ሲስተም በርቀት የሚገኙና በአገሪቱ በተመረጡ አካባቢዎች የሚገኙ 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል። 

በመርኃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የጤና ሚንስትር ተወካይ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ ፣በኢትዮጵያ የአለም አቀፉ የክትባት ጥምረት (ጋቪ) ከፍተኛ ባለሙያ ታባኒ ማፖሳ፣ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፖን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል። 

በዚህ ወቅት የጤና ሚንስትር ተወካይ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በአገሪቱ ያሉ 305 ጤና ተቋማትን ተጠቃሚ በማድረግ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል። 

የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት። 

በኢትዮጵያ የአለም አቀፉ የክትባት ጥምረት (ጋቪ) ከፍተኛ ባለሙያ ታባኒ ማፖሳ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአራት አገራት የሚገኙ 1 ሺህ የጤና ተቋማትን የፀሀይ ታዳሽ ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ በተቋሙ የተያዘው የ35 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት አካል መሆኑንም ገልጸዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም