የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን መጻኢ ጊዜ ለመወሰን የጋራ ትብብራቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል -አምባሳደር ረታ ዓለሙ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን መጻኢ ጊዜ ለመወሰን የጋራ ትብብራቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል -አምባሳደር ረታ ዓለሙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን መጻኢ ጊዜ ለመወሰን የጋራ ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ረታ ዓለሙ ገለጹ።
የአፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች እና በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ኮንፍረስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
"አፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች፤ በዓለም አቀፍ ውድድር ካሉ እድሎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ" የኮንፍረንሱ መሪ ሃሳብ ነው።
ኮንፍረሱን ያዘጋጁት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የአልጄዚራ የጥናት ማዕከል ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ረታ ዓለሙ በዚሁ ወቅት የአስተዳደር ስርዓት እና ብልሹ አሰራሮችን ጨምሮ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የአፍሪካ ተጋላጭነትና ፈተናዎች መንስኤ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዓለም ኃያላን አገራት የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት መሰረት አድርገው በአህጉሪቱ የሚያደርጉት ፋክክር ትልቅ ፈተና መፍጠሩን አመልክተዋል።
የአፍሪካ አገራት ያሉባቸውን ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎች ለመቋቋም ያላቸውን አቅም እና ሀብት በማስተባበር መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትስስር ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቅሰው መሰረተ ልማት አህጉራዊ ትብብርን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
አፍሪካ የራሷን የሰላምና ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በራሷ መምራት እና ማስተዳደር እንደሚገባት አመልክተዋል።
ለዚህም የአፍሪካ አገራት በጋራ መቆም እንዳለባቸውና የአፍሪካ ሕብረት በአህጉሪቷ ጉዳዮች ላይ ያለውን የመሪነት ሚና ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መግቢያ በር ናት ያሉት አምባሳደር ረታ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እንደምትጫወት ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዓለም ላይ ያለው የጂኦ-ፖለቲካ ፋክክር የፈጠራቸው ፈተናዎች የአፍሪካን የተጋላጭነት ፈተና እንዳባባሰው ገልጸዋል።
በዓለም ላይ ያሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች በአፍሪካ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የወጪ ንግድ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎች ማሳደራቸውን ተናግረዋል።
ድህነት፣ ግጭቶች፣ የሕዝብ እድገት፣ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ ጽንፈኝነት እና ሌሎች ፈተናዎች የአፍሪካን ተቋማዊ አቅም ደካማ ማድረጉን ነው አቶ ጃፋር የገለጹት።
የአፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኃይል ፋክክሩ የፈጠረውን ፈተና እና ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት አበክረው መስራትና ሚዛን ጠብቀው መሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ኮንፍረንሱ የአፍሪካን የተጋላጭነት ፈተናዎች ላይ መፍትሔ ለማበጀት እና በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ካሉ እድሎች ተጠቃሚ ለመሆን በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦች እንደሚቀርቡበት ተናግረዋል።
የአልጄዚራ የጥናቶች ማዕከል የጥናት ዘርፍ ኃላፊ ኢዘዲን አብደልሙላ(ዶ/ር) የዓለም ኃያላን አገራት በአፍሪካ ውስጥ ፋክክር የሚያደርጉት አህጉሪቷ ያላትን የተፈጥሮ እና የሰው ኃይል ሀብቶች መጠቀምን ግባቸው አድርገው መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ ፍላጎት ከቅኝ አገዛዝ እና ከቅኝ ግዛት እሳቤዎች የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል።
የኃይል ፋክክር እና የሰላምና ፀጥታ ፈተናዎች የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ችግር ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ናቸው ብለዋል።
አፍሪካ በዚህ ዓለም አቀፍ ፍላጎትና ፋክክር ውስጥ የባለብዙሃንና የሁለትዮሽ የትብብር ማዕቀፎችን በመጠቀም ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባት ጠቁመዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሰላም እና ደህንነት ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ መሉነህ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከዓለም አቀፍ የኃይል ሚዛን የበላይነት ፋክክር ጋር ተዳምረው የአፍሪካን የተጋላጭነት ፈተናዎች እንደጨመሩት ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሽብርተኝነትን እና ፅንፈኛ ቡድኖችን መዋጋት፣ የሰብዓዊ እና የደህንነት ፈተናዎችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የድንበር አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ተጋላጭነትን መቀነስ ፣ የናይል ወንዝን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችን በጋራ ማልማት ለአህጉሪቷ ዘላቂ መፍትሔዎችን ይዘው እንደሚመጡ አስታውቀዋል።
የዜጎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
ኢጋድ በቀጣናው ሰላም፤ ደህንነት እና ብልፅግና እንዲረጋገጥ ለአባል አገራት የአቅም ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከቀትር በፊት በነበረው መርኃ ግብር የእዳ ጫና በአፍሪካ አገራት ተጋላጭነትን ላይ ያሳደረው ፈተና፣ ሽብርተኝነት እና የባህር ውንብድና የፈጠሯቸው ስጋቶች፣ የአፍሪካ የድንበር ቀውሶች ውስጣዊ ፈተናዎች እና የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ፋክክር ፣በአፍሪካ ያሉ እድሎች እና ፈተናዎችን የተመለከቱ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ኮንፈረንሱ እስከ ነገ ይቆያል።