ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከግብርና ጋር ተደጋግፎ እንዲያድግ እድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተካሄዱ ተግባራት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከግብርና ጋር ተደጋግፎ እንዲያድግ እድል መፍጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።  

መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉትን ችግሮችን ለማቃለል ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል፣ ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። 

ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግብርናው መስክ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የግብዓት እጥረት እንዳይገጥመው ሰፊ አስተዋጽኦ አበርክቷል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንደገሉጹት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተካሄዱ ኢንሼቲቮች ግብርናውና ኢንዱስትሪ ዘርፉ ተደጋግፎ እንዲያድግ እድል ፈጥሯል። 

በተለይም በግብርናው ዘርፍ ኢንሼቲቭ ተቀርፁው የሚከናወኑ ተግባራት የኢንዱስትሪውን የግብዓት እጥረት በሚፈታና በዘርፉ የሥራ እድል ፈጠራ ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል ነው ያሉት።

በንቅናቄው የነባር ኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግና እንዲሁም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የተከናወኑት ተግባራት የግብርናውን ዘርፍ አብሮ እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቁመዋል። 

ንቅናቄው ኢንዲስትሪው ከግብርና ዘርፉ ምርትን በመቀበል አጠቃላይ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን የምርት ሂደት የሚያሳድግና ኢኮኖሚውን ጠንካራ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነትም በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ ዘርፍ ላይ የተጀመሩት ኢኒሼቲቮች በግብርናው እሴት ሰንሰለት ውስጥ አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።    

እንደ አገር የማምረት አቅም እያደገ የመጣ ቢሆንም አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ምርት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያለው ድርሻ ዝቅተኛ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ  ባለፉት ሁለት ዓመታት ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ታምርት የተሰጠው ትኩረትና ድጋፍ ዘርፉን በአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ማድረጉንም ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም