ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል 1ሺህ 250 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴና ማሽላ በኩታገጠም ለምቷል

ሐረር ፤ጥቅምት 1/2017 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል  በመኸር ወቅቱ በ1ሺህ 250 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴና ማሽላ  በኩታገጠም መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሬድዋን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በመኸር ወቅቱ በተለይ በሽታና ድርቅ ተቋቁሞ በሦስት ወራት ምርት የሚሰጥ “መልካም” የተሰኘ የማሽላ ዝርያ በ800 ሄክታር መሬት ላይ ለምቷል።

በክልሉ ኤረርና ሶፊ ወረዳዎች ላይ የለማው የማሽላ ዝርያ በሄክታር እስከ 43 ኩንታል ምርት የሚሰጥና ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ይጠቀም ከነበረው ዝርያ በእጥፍ ብልጫ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የማሽላ ዝርያውን በቀጣይ ከ6ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል።

በተመሳሳይ  ኪንግ በርድ የተሰኘ የስንዴ ዝርያ በ450 ሄክታር ኩታገጠም መሬት ላይ እየለማ መሆኑን ጠቁመው ዝርያው በሄክታር  35 ኩንታል ምርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል ።


 

በተለይ በክልሉ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ስንዴን በክላስተር ማልማት አዋጪ መሆኑን በመረዳት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ  ስንዴና ማሽላ ልማት ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን የማጠናከር፤ የተስተዋሉ እጥረቶችን ደግሞ በማረም የአርሶ አደሩን ምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ስራ   እየተሰራ መሆኑ አመልክተዋል።

በተለይ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማጎልበት ምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ በሚከናወነው ስራ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጉን አቶ መሀመድ ተናግረዋል።

"ባለፈው ዓመት በኩታገጠም ካለማነው ስንዴ 30 ኩንታል ምርት በግሌ አግኝቻለሁ " ሲሉ ያስታወሱት ደግሞ  የሶፊ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ በዳሳ ናቸው።

"ስንዴን ማምረት እራስን በምግብ ከመቻል ባለፈ በገቢም ደረጃ የተሻለ  በመሆኑ ዘንድሮም የተሻለ ምርት ለማግኘት በጋራ እየሰራን ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

ዘንድሮ የዘራነው ማሽላ ምንም ዓይነት በሽታ ሳያጠቃው  በአጭር ጊዜ ደርሷል፤ይህንንም ስራ በቀጣይ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ  የሶፊ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አሻ አብዲ ናት።

ከዘሩት ማሽላ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።

አርሶ አደር አህመድ ቃሲም በበኩላቸው "መልካም” የተሰኘ ማሽላ ዘርቼ በሶስት ወራት ጊዜ ደርሷል፤ ከዘራሁት ሁለት ሄክታር መሬት ላይም  እስከ 80 ኩንታል ምርት አገኛለው ብዬ እጠብቃለሁ"  ሲሉ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም