ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017 (ኢዜአ)፡- የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አዲስ ለተሰየሙት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሩሲያና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመልካም ባህል እና ወዳጅነት እንዲሁም የጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በፕሬዚደንትነት ዘመንዎ በሁሉም ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብራችንና ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ጥቅም መከበር የበለጠ እንደሚሰሩ አምናለሁ ብለዋል፡፡

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከርም እንዲሁ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በማመን የፕሬዚደንትነት ዘመንዎ ውጤታማ እንዲሆን እመኛለሁ ነው ያሉት፡፡


 

በተመሳሳይ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭም እንዲሁ ለፕሬዚደንት ታዬ አጽቀስላሴ እንኳን ደስ አልዎ የሚል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልካም ምኞት መልዕክታቸውም ፕሬዚደንት ታዬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው በሰሩባቸው ጊዜያት ሲያበረክቱ የነበረውን መልካም አስተዋጽኦ በአድናቆት ጠቅሰዋል፡፡

በፕሬዚዳንትነት የስልጣን ዘመናቸውም በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እና ለአፍሪካ አህጉር የጋራ ተጠቃሚነት በተባበሩት መንግስታት መድረኮች በተለይም በብሪክስ ላይ አስተዋጽዋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም