የህፃናት ማቆያ ለሴት የመንግስት ሰራተኞች ውጤታማነት - ኢዜአ አማርኛ
የህፃናት ማቆያ ለሴት የመንግስት ሰራተኞች ውጤታማነት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 1/2017 (ኢዜአ)፦የህፃናት ማቆያ ለሴት የመንግስት ሰራተኞች ውጤታማነት
የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ሴት የመንግስት ሰራተኞች በመውለዳቸው ምክንያት በስራቸው ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚፈጥርባቸውን እንቅፋት መፍታት እንደሚገባ ይደነግጋል።
ያለ ምንም ስጋትና ሀሳብ በሙሉ ኃይላቸው፣ ጉልበታቸው፣ እውቀታቸውና ጊዜያቸው ተጠቅመው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይረዳ ዘንድ ሁሉም የፌደራል የመንግስት ተቋማት የህፃናት ማቆያ ማዕከል ማቋቋም እንዳለባቸው እንዲሁ፡፡
በዚህም መሠረት አንዳንድ ተቋማት የህፃናት ማቆያ ማዕከል በመክፈት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ይታወቃል።
ተግባራዊ የተደረገው የህፃናት ማቆያም ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በርካታ የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የህፃናት ማቆያ ማዕከላት በመገንባት ዕድሜያቸው ከአራት ወር እስከ አራት ዓመት ያሉ ህፃናትን እየተንከባከቡ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የህጻናት ማቆያ ተጠቃሚ እናቶች በተቋማቸው የልጆች ማቆያ ማዕከል መኖሩ ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የህጻናት ማቆያ ተጠቃሚ የሆነችው ትእግስት ወርቁ የማቆያው መከፈት ስራዋን በአግባቡ ለማከናወንና ለልጇም ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ ለመስጠት እንዳስቻላት ገልጻለች፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የህጻናት ማቆያ ተጠቃሚ የሆነችው ፎዚያ ጄይላን በበኩሏ፤ ማቆያው በሴቶች ላይ የሚኖረውን ጫና በመቀነስ ትልቅ ዕረፍት እንደሚሰጥ በመግለጽ፤ በቅርበት ልጇን እየተንከባከበች በሥራዋም ውጤታማ መሆን እንደቻለች ነው የምትናገረው።
የተቋማቱ የህጻናት ማቆያ ሃላፊዎች በተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ የተደረገው የህፃናት ማቆያ ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የህጻናት ማቆያ አስተባባሪ ስንታየሁ ተድላ ማዕከሉ በ2010 ዓ.ም. በውስን ህጻናት ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
በተለይም በተቋማት የህጻናት ማቆያ መኖሩ ህጻናቱ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ከማስቻሉም ባለፈ እናቶችም ጊዜያቸውን በአግባቡ በስራ ላይ እንዲያሳልፉ እየረዳቸው ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሴ ኢደኤ በበኩላቸው ፤ የህጻናት ማቆያው በተለይ እናቶች ስራቸውን ተረጋግተው እንዲያከናውኑና ውጤታማ እንዲሆኑ እንደረዳቸው ተናግረዋል፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቋማት አካቶ ትግበራ ክትትልና ድጋፍ እና ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ከተማ ለገሰ በበኩላቸው፤ሚኒስቴሩ በተቋማት የልጆች ማቆያ ማዕከል የማስፋት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የህፃናት ማቆያ ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ስለመሆኑ ገልጸዋል።