የሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017(ኢዜአ)፦ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ለ17ኛ ጊዜ በመላው ሀገሪቱ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦ በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበርም ምክር ቤቱ ጠቅሷል፡፡
ዕለቱ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሥነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው፡፡
የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ ለብሔራዊ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ከፍታ እንዲሁም ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም እንዳለው መገለጹን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።