ቀጥታ፡

የዲጂታል ስርዓቱን ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ ለማድረግ ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል - አቶ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 1/2017 (ኢዜአ)፦  የዲጂታል ስርዓቱን ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ ለማድረግ ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የሀገርን ሉዓላዊነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።  

ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር " የቁልፍ መሠረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት " በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር በሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል። 

የሳይበር ደህንነት ወር እንደ ሀገር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እየተካሄደ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ21ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው። 

ለአንድ ወር በሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች እንደሚካሄዱም ተጠቁሟል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ የሀገርን ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሳይበር ደህንነት ቁልፍና ወቅታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የዲጂታል ሃብቶችን የመጠበቅ እና የዜጎችን ደህንነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ ለሳይበር ደህንነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ስርዓት ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ እንዲሆንም ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው የሳይበር ደህንነትን በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በሳይበር ቴክኖሎጂ ልማት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት በማገዝ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ማበልጸግ እንደሚገባም ጠቁመዋል። 


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዕቅድ መሠረት የሳይበር ደህንነትን ለመጠበቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሳይበር ደህንነት ወር መከበርም የዜጎችን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር የላቀ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ ከቢሊዮን ብር ኪሣራ መታደግ መቻሉንም አስታውሰዋል። 

እየተካሄደ በሚገኘው የመክፈቻ መርሐ ግብር የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሌሎችም እንግዶች ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም