ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታዋን ከብሩንዲ ጋር ታደርጋለች 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2017 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር ዛሬ ያደርጋል።
የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዛም ኮምሌክስ ስታዲየም ይከናወናል።
በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ 2 እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በዩጋንዳ 3 ለ 0 እና በደቡብ ሱዳን 2 ለ 1 ተሸንፏል።

ኢትዮጵያ ያለ ምንም ነጥብ እና አራት የግብ እዳ በምድቡ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች።

ተጋጣሚዋ ብሩንዲ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ደቡብ ሱዳን 1 ለ 0 ስታሸንፍ በዩጋንዳ 4 ለ 1 ተሸንፋለች።

ብሩንዲ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በዚሁ ምድብ አስቀድማ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባቷን ያረጋገጠችው ዩጋንዳ በተመሳሰይ ከቀኑ 10 ሰዓት በኪኖንዶኒ ሙኒሲፓል ካውንስል ስታዲየም ከደቡብ ሱዳን ጋር ትጫወታለች።

ዩጋንዳ ኢትዮጵያን 3 ለ 0 እንዲሁም ብሩንዲን 4 ለ 1 በማሸነፍ በስድስት ነጥብ እና በስድስት የግብ ክፍያ ምድቡን እየመራች ትገኛለች።

ተጋጣሚዋ ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን 2 ለ 1 ስታሸንፍ በብሩንዲ 1 ለ 0 ተሸንፋለች።

ደቡብ ሱዳን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ተጋጣሚዋን ብሩንዲን አራት እና ከዚህ በላይ በሆነ የግብ ልዩነት ማሸነፍ እና የደቡብ ሱዳን  በዩጋንዳ መሸነፍን ትጠብቃለች።

በተያያዘም በምድብ 1 ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ታንዛንያ ሱዳንን 1 ለ 0 ስታሸንፍ ሩዋንዳ እና ኬንያ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

በዚሁ ምድብ ታንዛንያ እና ሱዳን በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ኬንያ በ4 ነጥብ፣ ሩዋንዳ በ1 ነጥብ እና ጅቡቲ ያለ ምንም ነጥብ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በዚህ ምድብ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉ አገራትን የሚለዩ የምድብ ጨዋታዎች ጥቅምት 3 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄዱ ሴካፋ አስታውቋል።

የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።

በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም