የሀገሬ ጉዳይ ቢከነክነኝ ከውጭ አገር ወደ ሀገር ቤት ተመልሼ መከላከያን ለመቀላቀል ወሰንኩ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገሬ ጉዳይ ቢከነክነኝ ከውጭ አገር ወደ ሀገር ቤት ተመልሼ መከላከያን ለመቀላቀል ወሰንኩ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፡-'የሀገሬ ጉዳይ ቢከነክነኝ ከውጪ አገር ወደ ሀገር ቤት ተመልሼ መከላከያን ለመቀላቀል ወሰንኩ የሚለው ምልምል መሰረታዊ ወታደር ዶክተር ጳውሎስ ጊና።
ከኬኒያዊት እናቱ እና ከኢትዮጵያዊ አባቱ በጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ የተወለደ ወጣት ነው ጳውሎስ ጊና።
ከተወለደ ገና በስምንተኛ ወር በቤተሰቡ ስራ ምክንያት ወደ እናቱ ሀገር ጎረቤት ሀገር ኬኒያ ተሻገረ።
ከልጅነት እስከ ጉልምስና የልጅነት ትዝታ፣ የትምህርት ቤት ህይወቱን በኬኒያ በማድረግ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሞምባሳን ጨምሮ በተለያዩ የኬኒያ ከተሞች ተከታትሏል።
የህክምና ትምህርት ለሰባት ዓመታት ተከታትሎ ሜዲካል ዶክተር ጳውሎስ ተብሎ በመንግሥት ስራ ተቀጠረ።
የስራ ቋንቋው ኪስኻህሊ ሲሆን አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ አማርኛ እና ጋሞኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል።
ጳውሎስ ዕድገቱና ሁሉ ነገሩ ኬኒያ ቢሆንም 'ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለውጥም" እንዲሉ ሁሌም ሀገሩን በማሰብና በመውደድ ጭምር ኢትዮጵያዊነቱን አለቀቀም።
በተለይም በቀድሞ ጦር ሰራዊት አባል የሆኑት ወላጅ አባቱ ሻለቃ ጊና ግዴቦ፤ ስለኢትዮጵያ ታሪክና ባህል እያስተማሩ እና እየመከሩ ማሳደጋቸው የሀገሩ ፍቅር በውስጡ እንዲቀር እንዳደረገው ይናገራል።
'ሀገሬን በትዝታ የተሰኘ መፅሐፍ አባቴ የሰጠኝ መፅሐፍም ስለውትድርና ትልቅ አክብሮትና ፍቅር እንዲያድርብኝ አድርጎኛል ነው የሚለው።
ኬኒያ እያለሁ በየትኛውም አጋጣሚ ይሁን በቴሌቪዥን ስለኢትዮጵያ በማየውና በምሰማው ነገር ሀገሬን በውትድርና ማገልገል እንዳለብኝ እንድወስን አድርጎኛልም ሲል ይናገራል።
በትምህርቱ ዘልቆ የህክምና ዶክተር የሆነው ጳውሎስ ሀገሬን የማገልገል ምኞቴን ማሳካት አለብኝ በማለት
ኢትዮጵያን እስከ ሕይወት መስዕዋትነት ለማገልገል በሙሉ ፍላጎት ቁርጠኝነት ወደ ሞያሌ ማቅናቱን ያስታውሳል።
የኢትዮጵያ ማንነቱን ተላብሶ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ወስኖ ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ሲወስንም አባትም መርቀውና አመሰግነው ወደ ውትድርና ልከውታል።
የዶክተር ጳውሎስ የረጅም ጊዜ ህልም ተሳካ እና ለወታደራዊ ትምህርት ወደ ጦላይ የከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ገባ።
የስልጠና ቆይታውን በማጠናቀቅም በዛሬው ዕለት ተመርቆ ምልምል መሰረታዊ ወታደር ዶክተር ጳውሎስ ጊና ለመባል በቅቷል።
ከምርቃቱ በኋላ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታም በህክምና ሙያም ሆነ በውትድርና ሙያ ሀገሬን ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ ሲል አረጋግጧል።