አዲስ አበባ የትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ ምገባ ልምድና ተሞክሮዋን ለሚላን ከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት አባል አገራት አጋራች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ የትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ ምገባ ልምድና ተሞክሮዋን ለሚላን ከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት አባል አገራት አጋራች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፡- አዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ ምገባ ልምድና ተሞክሮዋን ለሚላን ከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት አባል አገራት አጋራች።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ስድስተኛው የ2024 የሚላን የከተሞች የምገባ ፖሊሲ ስምምነት ፎረም "የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም ለጤናማ እና ቀጣይነት ያለው የአፍሪካ ከተሞች እድገት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሲን ጨምሮ ከ40 በላይ የአፍሪካ አባል ከተሞች፣ የሚላን የከተሞች የምገባ ፖሊሲ ፓክት አስተባባሪዎችና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ እየተሳተፉ ነው።
በፎረሙ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ አዲስ አበባ ፎረሙን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በፈረንጆቹ 2022 በብራዚል ሬውዲጄነሮ ከተማ በትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም የምርጥ ተሞክሮ ዓለም አቀፍ የሞዴል እውቅና እና ሽልማት ያገኘች መሆኑን ተከትሎ ነው ብለዋል።
በዚሁ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በ255 ትምህርት ቤቶች ከ801 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከ16 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በመዲናዋ ከ36 ሺህ በላይ አረጋውያን የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን ለፎረሙ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የትምህርት ቤት ምገባው ተማሪዎች ስርዓተ ምግብ ተሟልቶላቸውና ጤንነታቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሊሴ በበኩላቸው ጣሊያን በምግብ፣ ደኅንነት፣ በአካባቢ ጥበቃና በትምህርት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው የልማት ትብብር ኩራት ይሰማታል ብለዋል።
አገራቸው ከኢትዮጵያ መንግስትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃና በትምህርት ቤት ምገባ ሥርዓት ላይ ጉልህ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
በአለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም የአፍሪካ ህብረት አለም አቀፍ ቢሮ ዳይሬክተር ሀመድ ኑሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው አለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም በአፍሪካ 66 ሚሊዮን ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።
በአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀጣይነት እንዲኖረው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ፣ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን ቢሮ ኃላፊ ኢዛቤላ ሉካፌሪ፤ ጣሊያን ለአፍሪካ ሀገራት የምታደርገው ድጋፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
የተማሪዎች ምገባ የምግብና የአካባቢ ደኅንነትን ተስማሚ በማድረግ ቀጣዩን ትውልድ የተሻለ ለማድረግ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ኤጀንሲው አፋርና ደቡብ ክልሎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ የሥነ-ምግብ ችግሮችን ለማሻሻል በትምህርት ቤት ምገባና ገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
የሚላን ከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት የከተማ ለከተማ ትብብር እና ምርጥ ተሞክሮ ልውውጥና በዘላቂና የከተማ የምግብ ስርዓት እንዲዳብር ለማድረግ እ.ኤ.አ በ2015 የተመሰረተ ስምምነት ነው።
አዲስ አበባ የሚላን የከተሞች የምገባ ፖሊሲ ፓክት በይፋ አባል ሁና የተቀላቀለችው በፈረንጆቹ 2021 ሲሆን 233 የዓለም ከተሞች የፎረሙ አባል ናቸው።