ጥራት ያለው ቡና በማምረትና እሴት በመጨመር የዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ይሰራል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፦ጥራት ያለው የቡና ምርትና ምርታማነትን በማስፋት እንዲሁም በምርቱ ላይ እሴት በመጨመር የዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበርና አምራቾች ገለጹ። 

አገራዊ የቡና ኤግዚቢሽንና የእውቅና መርኃ-ግብር ''ቡናችን ለብልጽግናችን " በሚል መሪ ኃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርኃ-ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት 8 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኞችን በመትከል ዘርፉን ለማሳደግ ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተናል ብለዋል። 

የኢኮኖሚያችን ዋልታ በሆነው የቡና ልማት 1 ሚሊየን ቶን የማምረት ግባችንን በመምታት አንፀባራቂ እድገት አሳይተናልም ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ጀና እንደገለጹት፤ ቡና አርሶ አደሩን ጨምሮ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚሳተፉ የዘርፉ ተዋንያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። 

ይህም ሆኖ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በቡና ምርት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ጀምሮ እስከ አገር ኢኮኖሚ የሚጠበቀውን ጥቅም ሲሰጥ አለመቆየቱን ነው ያነሱት።   

መንግሥት ለቡና ልማት በሰጠው ትኩረት የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የአገር ኢኮኖሚ ዋልታ መሆን የሚያስችል ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጋትን ቡና በጥራት እያቀረበች መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ የተፈጠረውን መነቃቃት ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት እውቅናና የሥራ መመሪያ ጥራት ያለውና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ምርት ለማቅረብ ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።  

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ፤ ድርጅታቸው ቡናና ሻይ አምርቶ ብዛት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተሸላሚ መሆኑን ገልፀዋል። 

የቡና ልማቱንና ግብይቱን በማዘመን ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን አበርክቶ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በገበያው የሚሳተፉ አካላትን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት። 

ይህንንም ከግምት በማስገባት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ፤ እሴት ጨምሮ በማቅረብ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።  

ቡና የአፍሪካ ሕብረት ስትራቴጂያዊ ኮሞዲቲ /መሠረታዊ ፍጆታ/ በመደረጉ የተሳለጠ የግብይት ሰንሰለት መፍጠር ማስቻሉን ገልፀዋል። 

ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ቡና በማምረት ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት አርሶ አደር ሙስጠፋ መሀመድ፤ የቡና ገበያው መሳለጡ እርሳቸውን ጨምሮ የቡና አምራቾችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም