ምክር ቤቱ ስድስት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን በመመርመር ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ስድስት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን በመመርመር ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን በመመርመር ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን የምክር ቤቱን 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ አዋጆች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ የተዘጋጁ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ ለምክር ቤቱ አመላክተዋል።
ረቂቅ አዋጆቹም የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣ የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ፣ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ፣ የኢትዮጵያ የህንፃ፣ የእንስሳትና ጤና እና ደህንነት ረቂቅ አዋጅ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ሃይሌ፤ የረቂቅ አዋጆቹን አስፈላጊነትና ያላቸውን ፋይዳ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
በተለይም የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ የሚቀርቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የዜጎችን የጤና አገልግሎት ፍትሕዊነትና ጥራት ለማሳደግም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም በተዘጋጁት ረቂቅ አዋጆች ዙሪያ ጥያቄና አስተያየቶችን በመስጠት የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴ አስፈላጊውን ምርመራ በማካሄድ በስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ምክር ቤቱም የእንስሳት ጤናና ደህንነት ረቂቅ አዋጅን ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን እና የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጆችን ለጤና፣ ማህበራዊ ልማት፤ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ ለከተማ፣ መሰረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል፡፡