ቀጥታ፡

ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ መሳካት ቻይና ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች- በአፍሪካ ህብረት የቻይና ተወካይ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፡- ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ መሳካት ቻይና ድጋፏን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የቻይና ተወካይ አምባሳደር ሁ ቻንግቹን ገለጹ።

የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኢንሼቲቭ ሙሉ ትግበራና የቻይና አፍሪካ የልማት ትብብር ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ውይይት ተካሂዷል።


 

በአፍሪካ ህብረት የቻይና ተወካይ አምባሳደር ሁ ቻንግቹን፤ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የልማት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሏን አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ የልማት ትብብሮችን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በትብብር መተግበር፣ የቻይና አፍሪካ የተባበሩት መንግስታት የትብብር ልህቀት ማዕከል እንዲቋቋም መስራት ከቀጣይ ትኩረቶች መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ጤና፣ ግብርና፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የአረንጓዴ ልማትና የጸጥታ መስኮች ላይም እንዲሁ።

ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ መሳካት ቻይና ድጋፏን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

ለረጅም ዘመናት የተሻገረው የአፍሪካ ቻይና ትብብር ለደቡብ ደቡብ ትብብር ምሳሌ እንደሆነ በአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሃመድ ቤልሆሲኒ ናቸው።


 

የዘላቂ ልማት ግቦችና አጀንዳ 2063 እውን በማድረግ የተሻለች ዓለምን ለአሁኑና ለቀጣይ ትውልድ ለመፍጠር ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ታጠናክራለች ብለዋል።

የቻይና አለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ሊቀመንበር ዛኦ ፈንግታኦ፤ የቻይና አፍሪካ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

ቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ትብብርና በደቡብ ደቡብ ትብብር ፈንድ በማቅረብ፣ በስልጠና እና ሌሎች የልማት ትብብር ዘርፎች እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

የአለም አቀፍ የልማት ትብብር ኢንሼቲቭ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እንደሚያግዝ ጠቅሰው እስካሁን 30 የአፍሪካ አገራት በይፋ መቀላቀላቸው ጨምረው ገልፀዋል።

ቻይና ለአለም አቀፍ የልማት ትብብር ኢንሼቲቭ ሙሉ ትግበራ እና የቻይና አፍሪካ የልማት ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ አገራት ለሚተገብሯቸው የልማት እስትራቴጂዎች ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት ዘርፎች ድጋፍ በማድረግ ትብብሩ እንደሚቀጥልም እንዲሁ።


 

የኢትዮጵያ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)፤ ቻይና በሮድ ኤንድ ቤልት ኢንሼቲቭ አማካኝነት ለኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታ ቁልፍ አጋር መሆኗን አስታውሰዋል።

በንግድ፣ ትምህርት፣ ስራ እድል ፈጠራና ሌሎች ዘርፍች ጠንካራ ትብብር እንዳላት ገልጸው በትምህርት ዘርፍ የሚደረጉ ትብብሮች በአለም አቀፍ የስራ ገበያ ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ማፍራት አስችሏልም ብለዋል።

አለም አቀፍ የልማት ኢንሼቲቭ በ76 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በቻይና ፕሬዝዳንት ዥ ቺንፒንግ አለም አቀፍ የልማት ትብብርን ለማጠናከር የቀረበ የልማት ኢንሼቲቭ ነው።

በውይይቱ አለም አቀፍ የልማት ድርጅት ተወካዮች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም