ቀጥታ፡

የአርባምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አርባምንጭ ፤ መስከረም 30/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደና  በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥራቱ በየነን ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት የከተማውን የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴን  የተመለከቱ ሲሆን፤ ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ ውይይትም አድርገዋል።


 

በከተማው በበጀት ዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ለማካሄድ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በውይይት መድረኩ ላይ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ፤  በአርባምንጭ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴው ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ባደረጉት የመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የጥራትና ፍጥነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ የከተሞችን ውበት በመጨመር ለነዋሪዎችና ቱሪስቶች ምቹ ከማድረግ ባሻገር የሥራ ባህልን የሚቀይርና ወጪን የሚቀንስ እንደሆነም ነው የገለጹት።

የኮሪደር ልማት ኢንሸቲቩ በሀገራችን ብሎም በክልላችን ከተሞችን በብዙ መልክ የቀየረና ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክት መሆኑም እየታየ ነው ብለዋል።

ለአርባምንጭ ከተማ ኮሪደር ልማት መሳካት የክልሉ መንግስት የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊና የአርባምንጭ ከተማ ኮሪደር ልማት አስተባባሪ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፤ በከተማው እየተገነባ ያለው የኮሪደር ልማት ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተጣምሮ መገንባት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።


 

ግንባታዎቹ የከተማውን የወደፊት ዕድገትና ስፋት ታሳቢ ያደረገ መሆን እንደሚገባውም ጠቅሰዋል።

የኮሪደር ልማቱ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድ ልማትና የቴሌ ተቋማት በተቀናጀ መንገድ እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።

የአርባምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት ስኬታማ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ከመንግስት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡም አቶ ጥራቱ  አስታውቀዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዳሙ ሻንበል እንደገለጹት፤ በከተማው በበጀት ዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት ከ11  ኪሎ ሜትር  በላይ  የኮሪደር ልማት ለማከናወን  ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም  ባለፉት ሦስት ወራት ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ  ወጪ 2 ነጥብ 32 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት መከናወኑን አስረድተዋል።

በልማቱ የተካተቱ አካባቢዎች ከዱንጉዛ አደባባይ እስከ አብሌ ጨዶ፣ ከጋሞ አደባባይ እስከ ድንጉዛ አደባባይ፣ ከጋሞ አደባባይ እስከ ኩልፎ ድልድይ እንዲሁም ውሃ ምንጭ ኮሪደር መሆናቸውን አንስተዋል።

በኮሪደር ልማቱ የእግረኞች መሄጃ ቴራዞ ንጣፍ፣ የውበትና የጥላ ዛፎች ተከላ፣ ማረፊያ ወንበሮችና የመብራት ዝርጋታ ሥራዎችን ያካተተ መሆኑን አቶ ገዳሙ አስረድተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣  የአዲስ አበባ ፣ የጋሞ ዞንና የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደሮች የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም