ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሴኡል ስማርት ሲቲ 2024 ምርጥ አመራር ሽልማት አሸናፊ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሴኡል ስማርት ሲቲ 2024 ምርጥ አመራር ሽልማት አሸናፊ ሆኑ
አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የሴኡል ስማርት ሲቲ 2024 ምርጥ አመራር ሽልማት አሸናፊ በመሆን እውቅና ተበርክቶላቸዋል።
ከንቲባዋ በዓለም ካሉ መሪዎች ከተማን ለመቀየር በትጋት በመሥራታቸው ልዩ እውቅና የሰጠው ውድድር በዓለም ዙሪያ ከ72 ሀገሮች እና ከ115 ከተሞች የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ያካተተ መሆኑም ተመላክቷል።
ከንቲባዋ የስማርት ሲቲ ምርጥ አመራር ሽልማት ተሸላሚ ሊሆኑ የቻሉት የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ህይወት ለማሻሻልና የከተማዋን መሰረተ ልማት ለማዘመን ባሳዩት ቁርጠኝነትና ባስመዘገቡት ውጤት መሆኑን በመረሀ ግብሩ አዘጋጆች ተገልጿል፡፡
ከንቲባዋ በተለይም እንደ ኮሪደር ልማት ባሉ ፕሮጀክቶች ለአየር ንብረት ተስማሚ ለሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ቅድሚያ በመስጠት ለሁሉም ነዋሪዎች ምቹ የሆነች አካታች ከተማ ለመገንባት በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማዋን ነዋሪዎችን ኑሮ በማሻሻል ላይ ትኩረት በማድረግ በሰሩት ስራና ባስመዘገቡት ስኬት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተደራራቢ ስራ ምክንያት በመረሀ ግብሩ ላይ መገኘት ያልቻሉት ከንቲባ አዳነች በተወካያቸው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሰለሞን አማረ በኩል ባስተላለፉት የምስጋናና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ጊዜያችሁን ጉልበታችሁን ሳትሰስቱ የከተማችንን እና የነዋሪዎቿን ህይወት ለማሻሻል ሌት ተቀን አብራችሁን የሰራችሁ ባለድርሻ አካላት እና ልማት የተባበራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ ውጤቱ የሁላችንም በመሆኑ ምስጋና ይገባችኋል ፤ ሽልማቱ የሁላችንም ነው ብለዋል።
እንዲህ አይነቱ ሽልማት ይበልጥ እንድንበረታ ፥ ተጨማሪ አቅምና ተነሳሽነት ይፈጥራልናል ይሄ ጅማሮ ነዉ ገና ብዙ እንሰራለን ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡