ቀጥታ፡

ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፦ ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን አዳዲስ የቡና ችግኞች መተከላቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሽንና የእውቅና መርኃ-ግብር ''ቡናችን ለብልጽግናችን " በሚል መሪ ሐሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ሁነት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ የቡና ልማት በጥራትና ምርታማነቱ አድጎ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም ከፍተኛ ጭማሬ እያሳየ መምጣቱን ገልፀዋል።

በአምራች አርሶ አደሮች 1 ኪሎ ግራም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ከ100 ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ከቡና የእሴት ሰንሰለት የሚያገኙት ድርሻም እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም በዓለም ደግሞ ሦስተኛ የቡና አምራች ሀገር በመሆን በተወዳዳሪነት መቀጠሏን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የጂ-25 ቡና አምራች ሀገራትን በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ የአፍሪካ 2063 ስትራቴጂክ የንግድ ምርት ሆኖ እንዲሰየም ለሕብረቱ ጉባዔ ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የትግበራ ሂደት በቀዳሚነት ወደ ግብይት ከሚገቡ ምርቶች መካከል ቡናን ቀዳሚ የሚያደርገው መሆኑን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር)፤ የቡና ልማትን ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የተጣጣመ በማድረግ ገቢውም እንዲጨምር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ድርሻ ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማደጉን ገልፀዋል።

በ2016 ዓ.ም. ሐምሌና ነሐሴ 82 ሺህ 853 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 377 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት እንደተቻለም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሽንና የእውቅና መርኃ-ግብር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎችም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የቡና አምራቾችና ላኪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም